Monday, 21 March 2016

ዳቦ ለተራቡ ፣ መሬት ለጠገቡ! (ታሪኩ አባዳማ)

ታሪኩ አባዳማ – መጋቢት 2008
“My village refused to move so they forced us with gunshots…”
Ethiopian farmer from Gambela region.
መሬት የዳቦ ምንጭ ነው። ሰማንያ በመቶ የሚሆነው ህዝብ በገጠር አራሽ የሆነባት ለሟ ኢትዮጵያ ዛሬ ሀያ ሚሊየን የሚደርሱ ዜጎቿ ዳቦ ለማኝ ናቸው። ገበሬ ሆኖ መሬት ከሌለው እሱ ብቻ ሳይሆን አገሪቱም ዳቦ የላትም – መሬትህን ከተቀማህ ትራባለህ – መሬትህን የቀማህ መንግስት ከሆነ ደግሞ በረሀብ እንድትሞት አስቀድሞ ፈርዶብሀል ማለት ነው።Ethiopia's Land Grabs
ወያኔ መሬትህን ሲቀማ ቀጠሮ አይሰጥህም… ረሀብ ቀጠሮ እንደማይሰጥ ሁሉ…
መሬቱን ተነጥቆ በረሀብ አለንጋ የሚገረፍ ገበሬ በራሱ ቄዬ ከሚፈስ ጅረት ውሀ ቀድቶ እንዳይጠጣ አፉ የተለጎመ ፣ እጁ የተጠፈረ ፍጡር ያህል ነው… ‘የአባይን ልጅ ውሀ ጠማው…’ ሲል ይገልፀዋል ያገሬ ሰው። የዳቦ ምንጭ የሆነውን እርሻ መሬት በባለቤትነት መቆጣጠር አለመቆጣጠር የመሆን አለመሆን ፣ የመኖር አለመኖር ጥያቄ ነው። ከዚህም በላይ ባህል ፣ ቋንቋ ፣ ታሪክ ፣ ማንነት እና ስነልቡና… ከመሬት ይዞታ ጋር እጅግ የተቆራኘ ግንኙነት አላቸው። መሬት ዳቦ ብቻ ሳይሆን ማንነትም ነው።
ወያኔ በቀየሰው ኢኮኖሚ ረሀብ እና ድህነት ህዝባችንን እያመሰው ይገኛል። ይህ አነሰ ተብሎ ጥይት እና እስር ፣ አፈሳ እና ድብደባ… በገጠርም በከተማውም ህዝብ ላይ ሀያ አምስት ዓመታት ሳያባራ ጭራሽ እየባሰበት ቀጥሏል። ሃያ አምስት አመታት ስልጣን ላይ ተቀምጦ ረሀብን ማስታገስ ያልቻለ መንግስት በ2025 ወደ መካከለኛ ገቢ እርከን ከፍ ትላላችሁ እያለ ያላግጥብናል።
በሚሊየን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዳቦ ከቶውንም ብርቅ በሆነበት በዚህ ዘመን በሚሊየን የሚለካ ለም መሬት ለጠገቡ ዘራፊዎች investors በወጉ ተለክቶ ሳይሆን ከዚህ ከዚያ ተራራ በመለስ በሚል የወፍ በረር ግምት ልቅ አግበስባሽነት (land grab) ሲሰጥ ቆይቷል። ከህንድ የመጣው ካሪቱሪ የተሰኘው መሬት አግበስባሽ ጋምቤላ 300ሺህ ሄክታር ለም መሬት በነፃ ተሰጠው ሲባል እውን የወያኔ ‘መሀንዲሶች’ በወጉ ለክተው የደረሱበት ስፋት ሆኖ አይደለም። ወያኔዎቹ ለዚህም የሚጨነቅ ህሊና ያላቸው ሰዎች አይደሉም።
ወያኔዎች የሚነድፏቸው የፖለቲካ ወይንም ኢኮኖሚ አቅጣጫዎች በአገር እና ህዝብ ላይ ለሚያስከትሉት አሉታዊ መዘዝ ቅንጣት ደንታ የላቸውም። ይህ ደግሞ ከጭፍን ድንቁርናቸው ብቻ ሳይሆን አለጠግብ ባይ ባህሪያቸው ብሎም ጠመንጃ ያሳበጠው እብሪታቸው ካስከተለው ዝርክርክት ጋር ተዳብሎ የመጣ ነው።
ላንድ ባለሀብት አንድ ግዙፍ የአገር አካል ቦድሰህ ስትሰጠው መሬቱ ላይ ያለውን ሰው ፣ እፅዋት ፣ ደን እና አራዊት እንዳሻህ አድርግ የሚል ሙሉ ስልጣን አስታቀፍከው ማለት ነው። ካሪቱሪ ያሻውን ያህል ደን ቢመነጥር ፣ ጫካ ቢያቃጥል ፣ አርሶ አደሮችን ቢያፈናቅል ወይንም የራሱን እስር ቤት አደራጅቶ አልፈናቀልም ፣ መሬቴን አለቅም ያሉ ዜጎችን ቢያጉርበት አንዳችም ተጠያቂነት እንደሌለበት ዋስትና እንዳለው ለማረጋገጥ ያህል 300ሺህ ሄክታር በፊርማ ፀድቆለታል። 100 ኪሎ ሜትር በ30 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ትንሽ አገር ቢጤ ግዛት ተከልሎለታል ማለቱ ይቀላል።
ካሪቱሪ ከዚያ ማዶ ተራራ እስከ ወዲያኛው ማዶ ሸንተረር ጀርባ በተንጣለለው ማሳ ፣ ደን እና ቁጥቋጦ የ300ሺህ ሄክታር ባለቤት አድራጊ ፈላጭ ቆራጭ ያደረገውን የወያኔ ሰነድ እያሳየ ባሻው መንደር መሬት ገልባጭ ዶዘር ይዞ ገብቶ መዝጊያ እየገለበጠ ነዋሪውን ቢያፈናቅል ተጠያቂ አይደለም። እስከ ዛሬ ሲፈፅም እንደቆየው ሁሉ ደን ጨፍጭፎ ዛፍ ቸበችቧል ፣ እንኳን ሰው የዱር እንሰሳት ሳይቀሩ ተሰደዋል… ደግሞም የ300ሺ ሄክታር መሬት ካርታ ባለቤት መሆኑ ከኢትዮጵያ ባንኮች በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ለመበደር ብቁ አድርጎታል።… ድንቄም ባለሀብት… የተቀማ መሬት አስይዞ ከባንክ ብድር። አገሪቱ ምን ያህል በወሮበሎች እየተመዘበረች መሆኗን ይህ ብቻ በቂ ማሳያ ነው።
ለመሆኑ 300ሺህ ሄክታር ስፋቱ ምን ያህል ነው ብላችሁ ገምታችሁ ታውቃላችሁ? በግርድፉ ስንወስድ 3ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ማለት ነው – አዲስ አበባ ስፋቷ 570 ስኬዌር ኪሎ ሜትር ነው። ለንፅፅር ይረዳ ዘንድ ጎረቤታችን ጂቡቲ አጠቃላይ ስፋቷ 23,200 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ይሆናል።  ካሪቱሪ በወያኔ ስጦታ አዲስ አበባን 6 እጥፍ የሚበልጥ ፣ የጂቡቲን አንድ ሰባተኛ የሚያህል ለም መሬት እጁ አስገብቷል ማለት ነው። ካንድ አገር ትንሽ የሚያንስ ከትልቅ ከተማ ደግሞ እጅግ ሰፋ ያለ መሬት ማለት ነው።
ብትችሉ ጉግል አድርጉና ስሌቱን ድረሱበት – – አላሙዲ ጋምቤላ ላይ ብቻ 10ሺ ሄክታር መሬት ቀምቷል – 10 ኪሜ በ10 ኪሎ ሜትር ማለት ነው (100ኪሎሜትር ስኩዌር)። ቢኤችኦ 27 ሺሕ ሔክታር፣ ሩቺ 3,500 ሔክታር፣ ኬናን 10 ሺሕ ሔክታር፣ ኤስኤንድፒ 50 ሺሕ ሔክታር መሬት ያገኙት በጋምቤላና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ውስጥ ነው… በየ ክፍለ ሀገሩ የተንጣለለው የነ ሀጎስ እርሻ ሲታከል ስፋቱ የት እየለሌ ነው…
ቦብ ጌልዶፍ የተባለው ዝነኛ እንግሊዛዊ አቀንቃኝ ወያኔን በወታደራዊ ትጥቅ ለማጠናከር የሚረዳ 100 ሚሊየን የሚደርስ ዶላር የለገሰው ገና ጫካ ሳሉ እንደሆነ ሁላችሁም ታውቃላችሁ። ጌልዶፍ ውለታው መሬት አልወደቀም – ዛሬ እሱም ሰፊ የወይን እርሻ መሬት ባለቤት ሆኗል። 8 miles በሚል ስም የሚጠራው የጌልዶፍ ኩባንያ በመንግስት ይዞታ ስር የነበረውን አዋሽ ወይን ጠጅ ከነሰፊ ማሳው በቁጥጥሩ ስር አውሎ ‘እያለማ’ ነው። የወይን ጠጅ ምርታችንን በጥራትም በብዛትም ለማሳደግ ዘፋኙ ባለውለታ ሀላፊነት ተሰጥቶታል…
ይህን ሁሉ መሬት የተቀራመቱ ስግብግብ ዘረፊዎች መሬቱን ምን እንዳደረጉት ጥናት ያካሄዱ አሜሪካዊ ምሁር የሚከተለውን ሪፖርት አቅርበዋል…
More than 60% of crops grown on land bought by foreign investors in Ethiopia is intended for export, instead of for feeding local communities… the land is used to grow profitable crops – like sugarcane, palm oil, and soy. The benefits of this food  production “go to the investors and to the countries that are receiving the exports, and not to the benefit of local communities” Paolo D’Odorico, professor of environmental science at the university of Virginia.
(ውርስ ትርጉም) – ለባዕዳን ቱጃሮች ከተቸረው መሬት ከ60% በላይ የሚሆነው ምርት አገር ውስጥ ላለው ተመጋቢ ሳይሆን ለውጪ ገበያ ታስቦ እና ትርፋማነቱ ተሰልቶ የተመረተ ነው። መሬቱ ላይ የሚመረተው እንደ ስኳር ፣ የዘንባባ ዘይት እና ሶይ (በህንድ እና አረብ እንዲሁም በሩቅ ምስራቅ ተፈላጊነት ያለው) ምርት ነው። ከዚህ ምርት ቀጥተኛ ተጠቃሚው መሬት የዘረፉት ባለሀብቶች እና የምርቱ ተቀባይ የሆኑት አገራት ብቻ ናቸው። መሬቱን አሳልፈው የሰጡት ህሊና ቢስ ወያኔዎች ምን እንደሚጠቀሙ በዚህ ጥናት አልተጠቀሰም።
በዚህ ጭካኔ የተመላበት ወረራ ለም መሬቶች ለቅርምት ፣ ዜጎች ደግሞ ለእንግልት ፣ ለድህነት ተዳርገዋል። ዜጎች ከተፈጥሮ አከባቢያቸው በሀይል በጠመንጃ ተገደው ወደ ማያውቁት ፣ ለኑሮ ጨርሶ ተስማሚ ወዳልሆነ ስፍራ ተግዘዋል። የማፈናቀሉ ዘመቻ አፈፃፀም እጅግ ሰብአዊነት የጎደለው መሆኑን ለመግለፅ ያስቸግራል። እርምጃው ዛሬም አልተገታም… ወያኔ በስልጣን ላይ እስካለ ወረራው አይገታም።
አኑርዳህ ሚተል የሚባሉት የኦክላንድ ምርምር ተቋም ዋና አስተዳዳሪ ባለፈው  ዓመት ባቀረቡት ሪፖርታቸው ስለ ኢትዮጵያ የመሬት ቅርምት ሲገልፁ…
“investors (እነኝህ ባለሀብቶች) በኦሞ ሸለቆ የተንጣለለውን መሬት ወስደዋል። በደን የተከበበውን መሬት መርጠው ደኑን መንጥረው አካባቢውን ዱር አድርገውታል። ደን የተጨፈጨፈው ለልማት ነው ይላሉ ግን እኔን የማይገባኝ የተፈጥሮ ደን ምንጠራ እንዴት ከልማት ጋር እንደሚዛመድ ነው”
“The investors take land in the Omo Valley. They clear all land, choose the best place where trees are, leaving the area open. They say it is for development, but they are clearing the forests. I wonder how to reconcile development with forest destruction.”
ጣሊያናዊው የፎቶ ጋዜጠኛ አልፍሬዶ ቢኒ በበኩሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ተዘዋውሮ ያገኘውን ሲያብራራ
 “These companies – mostly Saudi and Indian – are signing deals with the Ethiopian government to lease this land… for 25, 30 sometimes 50 years, depriving local population of the ability to harvest their crops and feed themselves. The government says the lands are empty and being harvested but from what I saw and documented in my reporting this is entirely not the case” Alfredo Bini an Italian photojournalist.
(ውርስ ትርጉም) “የኢትዮጵያ መንግስት ለም መሬቶችን ለሳውዲ እና ህንድ ኩባንያዎች ለ25 30 አንዳንዴም 50 አመት ለሚደርስ ኮንትራት (በባኮ ሲጋራ ዋጋ ነው ያለው መቶ አለቃ ተስፋ ገብራብ) ፈርሞ አስረክቧል። ይህን መሬት አርሰው ራሳቸውን ይቀልቡ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከአካባቢው ተባረዋል። መንግሰት ቦታው ጠፍ ነበር ማንም አይኖርበትም ነበር ይላል እኔ ባደረኩት ጥናት በደረስኩበት ጭብጥ ግን ይህ ፍፁም ውሸት ነው”።
የወያኔ ቀጣፊ ተፈጥሮ መላው አለም እንዲህ በይፋ እስከሚዘግበው ይፋ የሆነ ጉዳይ ነው። ዛሬ ጭራሽ ድንብርብራቸው ወጥቶ አንዱ ባለስልጣን የተናገረውን ሌላው እየተቃረነው ከዚህ ከዚያ ሲላተሙ እያየን ነው።
ሀያ ሚሊየን ህዝብ ላስቸኳይ የምግብ እርዳታ መጋለጡን በማያሻማ ቋንቋ ለመናገር እንኳ ድፍረት አላገኙም። ከለም መሬቶች ላይ የመፈናቀሉን ብሎም የተንሰራፋው ረሀብ ምን ድረስ እንደሆነ ለመዘገብ ወደ ስፍራው መጓዝ አይቻልም – ሙከራ ያደረጉትን የውጪ ጋዜጠኞችም መንገድ ላይ ጠብቆ በማሰር እና ማንገላታት የወያኔ ስራ ሆኗል። ይህ በአፄውም ሆነ በደርግ ዘመን ያልተደረገ አፈና ነው። የቢቢሲው ዲምብልቢን ሆነ ሌሎች የውጪ ጋዜጠኞች በደርግ ዘመን ድርቅ በመታቸው አካባቢዎች አላንዳች ተፅእኖ ተዘዋውረው የረሀቡን አስከፊነት ለመላው አለም እንዲያሳዩ ሙሉ ትብብር መደረጉ ይታወሳል።
በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ዛሬ ለረሀብ የተጋለጡት ኤልኒኖ በተሰኘ የተፈጥሮ ሚዛን መዛባት ምክንያት ነው በሚል ወያኔ ሊራቀቅብን ይዳዳዋል። የተፍጥሮ አየር መዛባት የግድ ረሀብ አያመጣም – በአለም እጅግ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ታምር እያስመዘገብን ነን ከሚለው ጉራቸው ጋር ይህ እንዴት እንደሚታረቅ የሚያውቁት ወያኔዎች ብቻ ናቸው። ለማንኛውም ግን ህዝብ እንደ ቅጠል ከመርገፉ በፊት ተገቢው ሪፖርት በተለይ ነፃ በሆኑ የውጪ ጋዜጠኞች ሊጠናቀር ይገባዋል። አሜሪካንን ጨምሮ አንዳንድ ለጋሽ አገሮች ዳቦ ለተራበው ህዝብ ለማድረስ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል። እርዳታው ጊዜያዊ ማስታገሻ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ እንዳልሆነ እነሱም ሁሉም ያውቃል – ህዝብ በጠመንጃ አፈሙዝ ስር የባርነት ቀንበር ተሸክሞ እያለ ሰው ሰራሽ በሆነ የአስተዳደር በደል እና የተዛባ ሀብት ስርጭት ሳቢያ የተተከለውን የድህነት ነቀርሳ መንቀል አይቻልም።
ያንድን እጅግ ድሀ ህብረተሰብ መሠረታዊ የዕድገት ደረጃ ፈር ለማስያዝ ወይም ወደ ላቀ እርከን ለማድረስ መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ቀዳሚ ቅድመ ሁኔታ ነው። በህዝብ ዘንድ ታማኒነት ያለው ፖቲካዊ ሥርዓት ለማናቸውም ዕድገት ቁልፍ መሆኑን የምሥራቁም ሆነ ምዕራቡ አለም ዕድገት ታሪክ የሚያረጋግጥ መሆኑን ላፍታ ልንዘነጋ አይገባም። እንደ ወያኔ አይነት ከህዝብ ጋር አይጥ እና ድመት ድብብቆሽ የሚጫወት መንግስት ግዙፍ ጠባሳውን ለመሸፈን አንዱን ሲያነሳ ሌላውን ሲጥል ዘመን ይቆጥራታል እንጂ የህዝቡን ህይወት አዎንታዊ በሆነ አቅጣጫ ለውጦ ዕድገት ሊያሰፍን ይችላል ማለት ዘበት ነው።
ወያኔ ጎጠኛ ነው – በዚህም ፀረ ብሔራዊ ፀረ ኢትዮጵያ ነው ፤ ወያኔ በዜጎች ሰብአዊ መብት አያያዝ ረገድ አፋኝ፣ አማቂ እና ገዳይ በመሆኑ ሕዝብ እንደ ወዳጅ ሳይሆን እንደ ማናቸውም ጉልበተኛ  ገዢ ብሎም ከብሔራዊ ጥቅም አንፃር እንደ ጠላት የሚያየው ሀይል ነው። እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ከልደት እስከ ዛሬ ድረስ በህዝብ ዘንድ ከቶውንም አመኔታ ያጣ በሙስና የተበከለ ነው።
“Those basic human rights are not being upheld in Ethiopia. It is therefore urgent to make voices of those impacted heard.”  ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች የተጨፈለቁባት አገር ናት። ስለሆነም የአፈናው ሰለባ የሆኑ ህዝቦች ድምፅ እንዲሰማ ማድረግ የሁላችንም አጣዳፊ ተግባር ሊሆን ይገባል ይሉናል ታዛቢዎች።
አንዳንድ ነጋዴዎች እስር ቤት አላቸው ነው ያለው ሀይለማርያም? አገር የሚያህል ክልል ህገ-ወጥ በሆነ አግባብ አስታቅፈህ ወህኒ ቢገነባበት ምን ይገርማል? እነ ካሪቱሪ 300ሺ ሄክታር መሬት ግዛታቸውን ለማስከበር ፀረ ልማት ሀይሎችን የሚቆጣጠሩበት እና የሚያስሩበት እስር ቤት የግድ ያስፈልጋቸዋል…
ሰሞኑን ከወያኔ ዜና መዋዕል አንብቤ ያስደመመኝን ጉዳይ ላካፍላችሁ እና ሀተታዬን ልደምድም — ጉዳዩ የወልቃይት ፀገዴን ማንነት የሚመለከት ነው። ወያኔ በየጊዜው ዳቦ ፍለጋ ወደ ወልቃይት እየፈለሱ የመጡ የትግራይ ተወላጆችን ሰልፍ እንዲወጡ ያደርጋል –
እነኝህ ወልቃይት ፀገዴ ላይ ሰልፍ የወጡ ነዋሪዎች ካነገቡት መፈክር መካከል “በህወሃት መስዋትነት የተረጋገጠው ማንነታችን በጥቂት ፀረ ሰላም ሃይሎች አይደናቀፍም” ይላል። እንደ ሰልፈኞቹ እና አሰላፊዎቹ ከሆነ የወልቃይት ማንነት ህወሃት አስራሰባት አመታት ከመታገሉ በፊት አይታወቅም ነበር ማለት ነው። ወያኔ አስራሰባት አመት ታግሎ መስዋዕትነት ባይከፍል ኖሮ የወልቃይት ማንነት መና ቀርቶ በቀረ ነበር። እንደ ሰልፈኞቹ መፈክር ከሆነ ግን ማንነቱ አይታወቅ እንጂ ወልቃይት የሚባል ቦታ እና ሰዎች ድሮም ነበሩ – የሆኑ ሰዎች ፣ ማንነታቸው ያልተረጋገጠ ሰዎች ወልቃይት ውስጥ ነበሩ እንደማለት። ወያኔ ግን አስራ ሰባት አመታት ታግሎ ማንነት አጎናፀፋቸው…
“በህወሃት መስዋትነት የተረጋገጠው ማንነታችን በጥቂት ፀረ ሰላም ሃይሎች አይደናቀፍም” ይላሉ ዳቦ ፍለጋ መጥተው መሬት ቀማኛ የሆኑት ሰፋሪዎች።
በዚህ አያያዝ ጋምቤላ ላይ ካሪቱሪ የተረከበው የ300ሺ ሄክታር ክልል ማንነት ህንድ ነው ቢባል አሜን ብለን መቀበል ይጠበቅብናል ማለት ነው። ምክንያቱም በአስራሰባት አመታት የወያኔ መስዋዕትነት ባይሆን ኖሮ ካሪቱሪን ማን ጋምቤላ ያደርሰው ነበር? ካሪቱሪ አሁን የ300ሺ ሄክታር መሬት ባለቤት መሆኑ ተረጋግጧል – ካሪቱሪ ደግሞ ህንድ ነው። 300ሺ ሄክታር መሬት ያገኘሁት ህወሃት 17 ዓመታት ታግሎ በከፈለው መስዋዕትነት ነው ቢል ማን ይጠይቀዋል – ካገሩ ያመጣቸውን ህንዶች አሰልፎ ‘…ማንነታችን በጥቂት ፀረ ሰላም ሃይሎች አይደናቀፍም’ ቢልስ ምን ችግር አለው። ጋምቤላ ህንድ ፣ ወልቃይትም ትግራይ የሆኑት በአስራሰባት አመት የወያኔ መስዋዕትነት ነው ብለን ዝም እንድንል ይጠበቅብናል። ጋምቤላ የትግራይ ኩታ ገጠም አለመሆኑ በጅቶታል።
የማንነት ጥያቄ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተፈቷል ነው ያሉት ክቡር ጠ/ሚኒሰትሩ?
ወይ ነዶ!!   by: ecadforum

No comments:

Post a Comment