Thursday, 2 June 2016

ሕግ ሕገ ወጥ ሲሆን ምን ይደረጋል? (ይኄይስ እውነቱ)

ይኄይስ እውነቱ
በሕዝብ ፈቃድ የተመሠረተ (ዴሞክራሲያዊ) መንግሥት አንዱና ዋናው ምሰሶ የፍትሕ አስተዳደር ሥርዓቱ ነው፡፡ ይህም ሕግ የማውጣት፣ ሕግ የመተርጐምና ሕግ የማስፈጸም ተግባራትን፤ እነዚህን ተግባራት ለማከናወን ድርሻና ኃላፊነት በተሰጣቸው የመንግሥት አካላት መካከል የሚኖር መስተጋብርንና የርስ በርስ ቊጥጥርን፤ የሕግና የዳኝነት ርግጠኝነትንና ተገማችነትን/ተተንባይነትነ፤ ባጠቃላይ በሕግ የበላይነት መመራትንና በሕግ መተዳደርን ይመለከታል፡፡ እነዚህ በሌሉበት ባንድ አገር ሕግና ሥርዓት የለም፤ ሕግና ሥርዓት በሌለበት ዜጎች ለኑሮአቸውና ደኅንነታቸው ዋስትና የላቸውም፤ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት አይታሰብም፤ ነፃነትና መብት ቦታ አይኖራቸውም፤ ሠርቶ በግልም በጋራም ለመበልጸግ የሚያስችል ከባቢ አይኖርም፤ ኃይልና ጉልበት ይሠለጥናል፤ ባጠቃላይ ሕገ አራዊት ወይም ሥርዓተ አልበኝነት ይነግሣል፡፡ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ያለው እውነታ ይኸው ሥርዓተ አልበኝነት ነው፡፡
‹በሕግ አምላክ ሲባል ወራጅ ውኃ ይቆማል› የሚል ለሕግ ልዕልና ዕውቅና የሰጠ ማኅበረሰብ እና ሕግን የማክበር ትውፊት በነበረበት አገር፣ ዛሬ ሕግ የመጨቆኛ፣ ነፃነትና መብትን መንጠቂያ፣ የልዩነት አሳብን ማፈኛ፣ ዜጎችን ማሳደጃ፣ በማያቋርጥ ፍርሃት ውስጥ መክተቻ፣የአንድን ጎጠኛ ቡድን ጥቅምና ፍላጎት ማስጠበቂያ፣ ባጠቃላይ ራሱን ‹መንግሥት› ብሎ በሰየመ የወሮበሎች ቡድን ሕዝብን የማሸበሪያ፣ምን ቀረኝ ብሎ ለሚፈጽማቸው ወንጀሎች ‹ሕጋዊ› ሽፋን መስጫ መሣሪያ ሆኗል፡፡
የጎሣ ልክፍት የተጠናወተውና አገር በማጥፋት ላይ የተሠማራው ሕወሓት የተባለው የወንበዴዎች ቡድን ኢትዮጵያን የምታኽል ታላቅ አገር በጉልበት ከተቆጣጠረ ጀምሮ አገሪቱን በጫካ ‹ሕግ› (ሕገ አራዊት) እየገዛ ይገኛል፡፡
እንደ ማሳሳቢያ፡-
1ኛ/ በዚህ ጽሑፍ የሚቀርበው አሳብ አጠቃላዩን ደንብ/እውነታ (the rule) እንጂ ውሱንና ልዩ ሁኔታዎችን (exceptions) ስለማይመለከት ቅር የሚሰኙ አንዳንድ ወገኖች ቢኖሩ አስተያየቱን በዚሁ መንፈስ እንዲረዱልኝ ለማሳሰብ እወዳለኹ፡፡
2ኛ/ ፈላጭ ቆራጭ መንግሥታት የሚያወጧቸው ‹ሕጎች› ሕጋዊ ተቀባይነት (legitmacy) አላቸው/የላቸውም የሚለው አካዳሚያዊ ክርክር ለዚህ አስተያየት ከግምት ያልገባ መሆኑን ማከል እፈልጋለኹ፡፡
  • ዛሬ ‹ሕገ መንግሥት› የለም አገር ለመበታተን፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት፣ ዝርፊያን ሕጋዊ ለማድረግ ወንበዴዎቹ የተፈጣጠሙበት የይስሙላ የስምምነት ሰነድ እንጂ፤በመሆኑም የሚናድ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የለም፡፡
  • ዛሬ ‹ሕግ አውጪ› አካል የለም፡፡ ወንበዴዎቹ በአሻንጉሊትነት ያሰቀመጡት፣ ጌቶቹ በቅድሚያ ያቀነባበሩለትን እንኳ ባግባቡ መተወን የተሳነው፣ የዘረኞችን የጥፋት ተልእኮ በማኅተም የሚያፀድቅ ሆድ አደር ደናቁርት መንጋ ስብስብ እንጂ፤
  • ዛሬ ‹ሕግ ተርጓሚ› አካል ወይም ዳኝነት የለም፡፡ ከሕግ በላይ የሆኑት ወንበዴዎች በሚሰጡት ቀጭን ትእዛዝ/ የፖለቲካ ውሳኔ ለማስፈጸም ወይም የንቅዘት አባሪ ተባባሪ ለመሆን በወንበዴዎቹ ተመርጠው በፍትሕ የሚያላግጡ ኅሊና ቢሶች እንጂ፤ ዛሬ ‹ሕግ አስፈጻሚ› የለም፡፡ ከአውራ እስከ ግልገል ባለሥልጣን ዜጎችን ማጉላላት/ደም እምባ ማስለቀስ ዋና ተግባሩ የሆነበት፣ በንቅዘት የተጨማለቀ፣ለወንበዴዎቹ በሎሌነት አድሮ ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት የሚል፣ የይስሙላውን ‹ሕግ› እንኳ ቦታ እንደሌለው በይፋ በተግባር የሚገለጽበት፣ በተለይም ‹ከፍተኛ አስፈጻሚ› ተብዬው ለጥፋት ዓላማው ‹ሕግ አውጪ› እና ‹ዳኝነቱን› ጠቅልሎ የያዘበት፣ አስተዳደራዊ ፍትሕ የጠፋበት፣ ‹መንግሥት› እና ፓርቲው (ሕወሓት) ያልተለዩበት፣ ባጠቃላይ የ‹መንግሥት› አሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት አለመኖር ዋና ማሳያ የሆነበት አካል እንጂ፤
  • ዛሬ ሕግና ዳኝነት በሌለባት ኢትዮጵያ ‹መንግሥት› የለም ሕወሓት የተባለና በዓለም አቀፍ ተቋማት በሽብርተኝነት የተመዘገበ ዘራፊና ወንጀለኛ የወሮበሎች ቡድን እንጂ፤
  • ዛሬ ወያኔ ጫካ ካቀነባበረው ከይስሙላ ‹ሕገ መንግሥቱ› ጀምሮ በየደረጃው የሚያወጣቸው ‹ሕጎች› በአብዛኛው ሕገ ወጥ ናቸው፡፡
በወያኔ አገዛዝ በየዓመቱ በአማካይ ከ50-60 የሚደርሱ ‹ሕጎች› ይወጣሉ፡፡ ከሚወጡት ‹ሕጎች› ውስጥ ዋና ዋናዎቹን በቅርበት የሚመረምር ታዛቢ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የአምባገኑን አገዛዝ ህልውናና ጥቅም በማስጠበቅ ዓላማ የሚቀረፁ መሆናቸውን በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ አንባቢን ማሰልቸት ስለሚሆን ሕገ ወጥ የሆኑትን ‹ሕጎች› መዘርዘሩ አስፈላጊ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ወያኔ በቅርቡ ሊተገብራቸው ያሰባቸው (ንጹሐንን መወንጀያና የራሱን ወንጀሎች መሸፈኛ) የኮምፒዩተር ወንጀል እና የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ‹ሕጎች› ረቂቅ የሕግ ወጥ ሕጎቹ አካልና ለሕግና የሕግ የበላይነት ያለውን ንቀት ቀጣይነት ማሳያ ናቸው፡፡ ታዲያ ‹ሕግ› ሕገ ወጥ ሲሆን ምን ይበጃል? መልሱ ቀላል ይመስላል፡፡ የሕግ የበላይነት የሚረጋገጥበት፣ በሕዝብ ተቀባይነት ያለውና ዜጎችን በእኩልነት የሚያስተናግድ ሕገ መንግሥታዊ ዲሞክራሲ/ሥርዓት መመሥረት ነው፡፡ መልሱን ተከትሎ የሚነሳው ‹እንዴት?› የሚለው ጥያቄ ግን እጅግ ከባድ ነው፡፡ የብዙዎች ዜጎችን ሕይወት እያስገበረ ነው፤ ብዙዎችን ፈቅደውና መርጠው ባላመጡት ማንነት ምክንያት የጅምላ ጭፍጨፋ ሰለባ እያደረገ ነው፤ ሚሊዮኖችን ለረሃብና ለችጋር እየዳረገ ነው፤ ኢትዮጵያውያንን ነፃነትና መብት አሳጥቶ በወህኒቤቶች እንዲማቅቁ እያደረገ ነው፤ ብዙዎችን ለስደት እየዳረገ ነው፤ ባጠቃላይ የአገሪቱንኅልውና እየተፈታተነ ነው፡፡
ስለሆነም በሕግ የበላይነት የምትተዳደር፣ ህልውናዋ የተጠበቀ አዲሲቱን ኢትዮጵያ ለማየት የምንፈልግ ኢትዮጵያውያን ኹሉ ይህን መረን የወጣ ‹ሥርዓት› በኅብረትና ኃላፊነት በተሞላው ሁለንተናዊ ትግል ማስወገድ ግዴታችን ነው፡፡
ዛሬ በየትኛውም የአገራችን ክፍል የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ለዘመናት ባደረገው መስተጋብር ያካበታቸው መልካም ባህሎች፣ ትውፊቶች፣ ልማዶች፣ ማኅበራዊ ጥሪቶች፣ ባጠቃላይ እሴቶች በዚህ ነውረኛና የባለጌዎች ‹ሥርዓት› በእጅጉ እየተሸረሸረ መሆኑ ባይካድም፣ የጥቂት ዘረኞችን መሠሪ ተልእኮና ጫና ኹሉ ተቋቁሞ በጨውነት እንዲመላለስ፣ ባንድነቱ ፀንቶና ተከባብሮ እንዲቆይ ያደረገው የሕግ መኖር አይደለም፡፡ ይልቁንም (እስላምም ሆን ክርስቲያን) እግዚአብሔርን በመፍራት/በማክበር ላይ የተመሠረተው እምነታችን፣ መልካም ባህላችንና ማኅበራዊ ደንቦች መሆናቸውን ብዙዎች የሚስማሙበት ይመስለኛል፡፡ የአገዛዙ ‹ሕግማ› ለኑሮው ሥጋት እንጂ ለሕይወቱ፣ ለደኅንነቱ፣ ለንብረቱ ዋስትና እንዳልሆነ ብዙ ታዝበናል፡፡ የሕግና ሥርዓት አምላክ ለፍትሕና ለነፃነት በየአቅጣጫው የሚደረገውን ሁለንተናዊ ትግል ለፍሬ አብቅቶ በሕግ የበላይነት የምትመራና የምትተዳደር ኢትዮጵያን ለማየት ያብቃን፡፡by: ecadforum

No comments:

Post a Comment