Thursday, 30 June 2016

የአማራ ብሄርተኝነት በመለክ ሃራ (ሊነበብ የሚገባው)

ይህ ጽሁፍ የድንቁ ወንድማችን መለክ ሃራ ስጦታ ነው።እንግድህ ይሄን በትእግስ ማንበብ ፣መረዳት እና መተግበር የኛ ስራ ነው ። መልካም ንባብ
=======================================================
የአማራ ብሄረተኝነት መስመር.... (1)………ስለ አማራ ማንነት
**************************************************
የአማራ ብሄረተኝነት በአማራ ነገዳዊ ማንነት እና ፖለቲካዊ አካልነት ላይ ያጠነጥናል፡፡ ለዛሬ ነገዳዊ ወይም ብሄራዊ ማንነቱን ተንትነን በማየት ፖለቲካዊ ማንነቱን በይደር እናቆያለን፡፡
አማራ ስንል አማራ የሚባለውን ህዝብ ማለታችን ነው፡፡ ታዲያ አማራ መሆን እንደምንድነው ቢሉ በሁለት ይመደባል፡፡
አንደኛው በዝርያ አማራ የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል ይመለከታል፡፡ ከጥንት የአማራ የዘር ሀረግ ያለው ህዝብ እና አማራ በመባል ሲጠራ የቆየው ህዝብ ማለት ነው፡፡ አማራ ስንል ሱዳን ያልሆነ፤ ጋምቤላ ወይም ጉምዝ ያልሆነ፤ ኦሮሞ ወይም ሱማሌ ያልሆነ፤ ትግሬ ወይም ኩናማ ያልሆነ ማለት ነው፡፡ ከእነዚህ እና ከሌሎች አጎራባች ነገዶች አንጻር ሲታይ እነዚህን ያልሆነ ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ 86 ብሄረሰቦች (ነገዶች) አሉ፡፡ 85ቱ አማራ አይደሉም፡፡ አማራ 85ቱን አይደለም፡፡ እነሱ አማራ አይደሉም፤ አማራም እነሱን አይደለም፡፡ ስለዚህ አማራ የብቻው የሆነ ነገዳዊ ማንነት አለው፡፡ ይህ ዘር ሀረጋዊ አማራነት “እኔ አማራ ነኝ” የሚል ገጽ ሲኖረው የዚህ “እኔ አማራ ነኝ” ሌላኛው ጎን ደግሞ “እሱ አማራ አይደለም” የሚል ገጽ ይፈጥራል፡፡ ይህም አማራ ከራሱ አንጻር የአማራን ማንነት ሲያመለክት፤ ከሌሎች አንጻርም እንደዛው አማራነቱን ያመለክታል፡፡ ለምሳሌ ዳንኤል ብርሀነ “እኔ ትግሬ” ነኝ ሲል በሌላ ገጹ “እኔ አማራ አይደለሁም” ወይም “እነ ተመስገን ደሳለኝ ትግሬ አይደሉም” ማለቱ ነው፡፡ ከትግሬ አንጻር ትግሬ ያልሆነ ሁሉ አማራ ነው፡፡ አዲስ አበባ ሲመጡ ነው ከአማራ ሌሎች ብሄረሰቦች እንዳሉ የሚያውቁት፡፡ በእነሱ አለም አለም የትግሬ እና የአማራ ተብላ በሁለት ትከፈላለች፡፡ ሌላውም ዘወር ዘወር ብሎ ሌሎችን እስካላየ ድረስ እንደዛ ነው የሚለው፡፡ ባጭሩ ትግሬ ያልሆነ ሁሉ አማራ ነው--ከትግሬ አንጻር፡፡ አማራ ደግሞ ትግሬዎችን ትግሬ እንጅ አማራ ናቸው ብሎ አይቆጥርም፡፡ ለአማራ ኦሮሞም ኦሮሞ ነው፡፡ ሱማሌም ሱማሌ ነው፡፡ ስለዚህ አማራ ራሱን አረጋግጦ የሚያቆምበት ነገዳዊ ቦታው አማራ ነው፡፡ ሌላው ትግሬ የሆነውን ያህል አማራም አማራ ነው፡፡ ይህ የዘር ሀረጋዊ አማራነት የስሜት ትስስርን አዳብሎ የያዘ ነው፡፡ “እኔ አማራ ነኝ” ሲል አንድ ሰው በአእምሮው የሚሳለው አማራ የተባለ አካል ነው፡፡ ያ አማራ የተባለ አካል አማራ የሆነበት እና ከሌሎች የሚለይበት ባህርያትን የያዘ ነው፡፡ አማራነቱን ሲያመለክት ወደአእምሮው የሚመጣ ቀድሞ የተሳለ ምስለ አማራ አለ፡፡ እኔ አማራ ነኝ ሲል ያንን ምስለ አማራ ማመልከቱ ነው፡፡ ይህም የዘር ሀረጋዊ እና የስሜት አማራነት ሌሎች ባህላዊ፤ ስነልቡናዊ፤ ስነልሳናዊ፤ ገጸ መሬታዊ እና ታሪካዊ እንዲሁም አኗኗራዊ መገለጫዎችን በውስጡ እንዳዘለ እንረዳለን፡፡
ሁለተኛው ባህላዊ አማራነት ነው፡፡ ከአማራ ህዝብ ጋር ለረዥም ጊዜ የኖሩ እና የአማራውን ስነልሳን፤ ስነልቡናና ባህርይ ሙሉ በሙሉ የወረሱ እናም ከአማራነት ውጭ በሆነ ሌላ መንገድ ራሳቸውን ሊገልጹ የማይችሉ ናቸው፡፡ እነዚህ በአመዛኙ የቅርብ ጊዜ ማለትም ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ በኋላ የመጡ ክስተቶች ናቸው፡፡ ያም ማለት የኢትዮጵያ ህዝብ በተሰባጠረ መልኩ ከዳር እስከዳር ተንቀሳቅሶ መስራት እና የውትድርና አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የሌላ ብሄረሰብ አባላትም ወደአማራ አገር መጥተው መኖር እንደጀመሩ የሚታወቅ ነው፡፡ የእነዛ ሰዎች ልጆች እና የልጅ ልጆች አማራዊ ባህርይ የተላበሱ በመሆናቸው በራሳቸው ጊዜ አማራነትን ወስደዋል፡፡ ነገር ግን በቁጥር ደረጃ ከዋናው ከዘር ሀረጋዊው አማራ ጋር ሲነጻጸሩ እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም፡፡ ከአማራ አገር ውጭ በሆኑ ከተማ አካባቢዎች የተወለዱ እና በአማራው ባህላዊ መሰረት ታንጸው ያደጉ እና የአማራነትን ማንነት በራሳቸው ጊዜ የደረቡም አይጠፉም፡፡ የእነዚህ ቁጥር ግን ከ1983 ወዲህ ግልባጭ መልክ ይዞ ከአማራነት ሸሽተው ወደማለቁ ናቸው፡፡ ለምን ቢባል አማራ መሆን ጉዳት እንጅ ጥቅም እንደማያመጣላቸው ሲያውቁ በአማራነት የቀየሩትን የአያትና ወላጅ ማንነት እንደገና አንስተዋል ማለት ነው፡፡ በአማራ አገር ውስጥ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጀምረው የኖሩትም ከዚህ 1983 ወዲህ የአያት ቅድመ አያት ማንነታቸውን በመሻት አማራነትን ለጥቅም ሲሉ ለውጠዋል፡፡ ይህም እሳቤ ወደአንድ መደምደሚያ ያደርሰናል፡፡ እርሱም ዛሬ አማራ ነኝ ብሎ የሚኖረው ህዝብ ከሞላ ጎደል ዋናው የዘር ሀረጋዊ አማራ መሆኑ ነው፡፡ የባህል አማራዎች ሲሸሹት ማምለጫ የሌለው እውነተኛው አማራ በአማራነቱ ጸንቶ ተገኘ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዘመን አማራ ስንል በዋነኝነት የአማራ ዘር (ስነፍጥረታዊ ህልውና) ማለታችን መሆኑ ከትክክልነትም ከፍ ያለ ነው፡፡
አማራነትን በሳንሳዊ መስፈርት መመዘን ይቻላልን?
አወ፡፡ በሚገባ እንጅ፡፡ አማራነት ዘር ሀረጋዊም ሆነ ባህላዊ ህልውና እንደሚኖረው ከላይ አይተናል፡፡ ባህላዊ አማሮች እየጠፉ ዘር ሀረጋዊ አማሮች ብቻ በአማራነታቸው መቅረታቸውንም አይተናል፡፡ አንድን ብሄር ብሄር የሚያደርገው ታዲያ ምንድነው ብልን ስንጠይቅ የሚከተለውን መስፈርት እናገኛለን፡፡
በታሪክ
አማራ በአማራነቱ እንደህዝብ የሚወክለው ታሪክ አለው፡፡ አማራ ለብቻው የሰራቸው እና ሌሎች ብሄሮች የማይጋሩት ታሪካዊ ሂደቶችና ስኬቶች አሉት፡፡ አማራ ራሱ ብቻውን በተዋናይነት የነበረበት ታሪክ ለረዥም ጊዜ ነበረ፡፡ ያ ታሪክ አማራን አንድ አይነት ምስል ይፈጥርለታል፡፡ ስለታሪክ ባወሳን እና ባሰብን ቁጥር የሆነ ምስለ አማራ በእዝነልቡናችን ይመጣል፡፡ ታሪክን ብቻውን ነጥለን ስንወስድ የሆነ የአማራ ምስል እናገኛለን ማለት ነው፡፡ ይህም በስነሰብ የሳይንስ ዘርፍ አንድን ብሄር ወይም ነገድ በነገድነት ከሚገልጹት ነገሮች አንዱ የጋራ የሆነ ታሪካዊ ሁነት ሲኖር ነው የሚለውን መስፈርት ያሟላል፡፡ የአማራን ታሪካዊ ሂደቶች፤ ድል እና ውድቀትም ጭምር ጨምቀን በመውሰድ አንዳች የአማራ ምስል እንፈጥራለን፡፡ ያ ታሪካዊ ሂደትም አማራን እንደህዝብ በአንድ አሃድ ይገልጸዋል ማለት ነው፡፡
በስነልቡናዊ-ማህበረሰባዊ ባህርይ
አማራ የራሱ የሆነ የጋራ ስነልቡናዊ ባህርይ አለው፡፡ ከሸዋ ሮቢት እስከ ገላባት፤ ከወልቃይት እስከ ባሌ ድረስ ብንሄድ አማራ አንድ አይነት ስነልቡናዊ ባህርይ ተላብሶ እናገኘዋለን፡፡ ይህም አንድ አይነት ስነልቡባዊ ባህርይ ከአማራነት የተወረሰ እና በትውልዶች መካከል ሲቀጥል የቆየ እና የሚቀጥል ነው፡፡ በርካታ ስነልቡናዊ ባህርያትን በመዘርዘር የአንዱ አካባቢ አማራ ከሌላው አካባቢ አማራ ፈጽሞ አንድ እንደሆነ እንደርስበታለን፡፡ ይህም በስነሰብ የሳይንስ ዘርፍ አንድን ብሄር አንድ ከሚያደርጉት እና በብሄርነት ከሚገልጹት ነገሮች አንዱ የጋራ የሆነ ስነልቡናዊ-ማህበራዊ ባህርይ ነው የሚለውን ያሟላል፡፡ እንግሊዝኛው Common psychosocial makeup ነው የሚለው፡፡ ይህም ያ አንድ አይነት ስነልቡና የሚያጎናጽፈው አንድ አይነት ማህበራዊ ባህርይን የሚያመለክት ነው ማለት ነው፡፡ ከተመሳሳይ ስነልቡናዊ ባህርይ ተመሳሳይ ማህበራዊ ባህርይ ይፈጠርና ሁለቱ ተዳብለው አንድን ህዝብ ገላጭ አሀዶች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አማራ አንድ አይነት ስነልቡናዊ-ማህበረሰባዊ ህልውና አለው ማለት ነው፡፡ ይህንን አሀድ ነጥለን በመውሰድ ብቻ የአማራን አንጻራዊ ምስል መከሰት እንችላለን፡፡
በቋንቋ (ስነልሳን)
አማራ የራሱ የሆነ አንድ ቋንቋ አለው፡፡ እረሱም አማርኛ ነው፡፡ ስለዚህ በሳይንሱ አንድ አይነት ቋንቋ የሚናገር ህዝብ የራሱ የሆነ የብሄርነት ወይም የነገድነት ህልውና አለው የሚለውን ይህ አማርኛ ቋንቋ ይገልጸዋል፡፡ እዚህ ላይ በአማራ አገር ውስጥ ታዲያ ሌላ ቋንቋዎች አሉ እና እንዴት ነው ማብራራት የሚቻለው ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል፡፡ አወ፡፡ ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ አማሮች አሉ፡፡ ነገር ግን ሌሎች ቋንቋዎች በግንዱ አማራነት ውስጥ ንኡስ ቋንቋዊ ማንነትን ብቻ ይፈጥራሉ እንጅ በአጠቃላይ አማራነት ላይ ተጽእኖ አያመጡም፡፡ በሳይንሱ Dominant Culture and Subculture የሚባል ነገር አለ፡፡ ይህም ጽንሰ ሀሳብ የሚገልጸው በአንድ ግንድ ባህል ውስጥ ንኡሳን ባህላዊ እሴቶችም ሊኖሩ መቻላቸውን ነው፡፡ በእኛ ጉዳይ ግንዱ አማርኛ ቋንቋ ሲሆን ንኡስ ቋንቋዎች ደግሞ አማርኛ ያልሆኑቱ ናቸው፡፡ አማርኛ ለምን ግንድ ባህል ሆነ ተብሎ ቢጠየቅ ሁሉም ከአማርኛ ውጭ የሚናገሩ ሰዎች አማርኛን ይናገሩታል ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት በአማራ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ አንድ አይነት የጋራ ቋንቋ አለው ማለት ነው፡፡ ይህንንም ሳይንሱ እንደሚያስረግጠው አንድ ህዝብ የጋራ የሆነ አንድ ቋንቋ ካለው የብሄርነት ህልውናው የተረጋገጠ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በአማራ አገር ውስጥ ያለን ህዝብ በሞላ አማርኛ በጋራ ቋንቋነት ይገልጸዋል ማለት ነው፡፡ ይሄ ምናልባት በአማራ አገር ውስጥ ላሉ ንኡስ (መንደርተኛ) ፖለቲከኞች ላይዋጥ ይችላል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ከአማራ ወጥቶ ወደኦሮሞ ወይም ወደትግሬ ወይም ወደሱማሌ ቢሄድ ያለ አንዳች ጥርጥር አማራ መሆኑ በእነዛ በእግዳ ሰዎች ይታወቃል፡፡ አንድ አማራ ወደእነዚህ ቦታዎች ሄዶ “እኔ እኮ አማራ አይደለሁም….እንትን ቋንቋ ተናጋሪ ነኝ” ቢል የሚያምነው የለም፡፡ “አንተ አማራ ነህ” ነው የሚባለው፡፡ ንኡስ ባህል ወይም ቋንቋ እዛው አማራ አገር ውስጥ ልዩነት ለመፍጠር ያገለግላል እንጅ ከአማራ አገር ሲወጣ ዜሮ ምስል ነው ያለው፡፡ ያ ሰው ከአማራ አገር ሲወጣ አጠቃላዩን የአማራ ምስል ይዞ ነው የሚወጣው፡፡ ስለዚህ የአማራ አገር ህዝብ አንድ የሆነ ቋንቋዊ ማንነት አለው ማለት ነው፡፡
በምጣኔ ሀብታዊ ሁኔታና መንግስታዊ አመራር
አማራ እንደህዝብ በግብርና ላይ የተመሰረተ ኑሮ የሚኖር ህዝብ ነው፡፡ በአማራ ውስጥ ትላልቅ ቦታ ያላቸው ግብርናና መንግስታዊ አመራር ናቸው፡፡ በአማራ እዝነልቡና ከእያንዳንዱ ሰው በላይ መንግስት አለ፡፡ ህዝብን ያለመንግስት ማሰብ አይቻልም፡፡ ህግና ስርአት ከመንግስት ይመነጫል ብሎ ያምናል፡፡ በመሬት ላይ የተመሰረተውን ኑሮውን የሚቆጣጠርለትም ይሄው መንግስት ነው፡፡ አማራን ከመንግስትነት እና መሬት ጋር ካለው ልዩ ቁርኝት ተነስተን አንድ አይነት ምስለ አማራ ልንከስትለት እችላለን፡፡
በገጸ መሬታዊ አሰፋፈር
አማራ አንድ ወጥ እና ቅርጽ ያለው አሰፋፈር ያለው ህዝብ ነው-- የዛሬውን አሰፋፈሩን ስንመለከት፡፡ በታሪክ የራሱ የነበሩት እና በወራሪዎች የተዘረፉበትን ስንጨምርም ከሞላ ጎደል Compact የመሬት ገጽ ላይ የሰፈረ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ አማራ በተለየ አንድ ላይ ይኖር የነበረ እና አንድ አይነት ብቻ አሰፋፈራዊ እጣ ፋንታ የነበረው ህዝብ ነው፡፡ ለምሳሌ ትግሬ በሁለት አገሮች ውስጥ ይገኛል፡፡ አፋርም በሶስት አገሮች ውስጥ ይገኛል፡፡ ኦሮሞ ከአራት በላይ በሆኑ አገሮች ውስጥ ይገኛል፡፡ ጋምቤላም በሁለት አገሮች ውስጥ ይገኛል፡፡ አማራ ግን በኢትዮጵያ ብቻ እንጅ በሌላ በየትም አገር አይገኝም፡፡ ይህም ማለት ለረጅም ዘመናት አንድ ላይ ሰፍሮ የኖረ ህዝብ ነው ማለት ነው፡፡ ለረጅም ዘመናት አንድ ላይ በመኖሩም ከላይ የተዘረዘሩትን የጋራ የሆኑ ታሪካዊ ሁነት፤ ስነልቡናዊ-ማህበራዊ ባህርይ፤ እና ስነልሳናዊ እሴት በጋራ አበልጽጎ ኖረ፤ በእነሱም በአንድ ወጥ ህዝብነት ይገለጻል እንላለን፡፡ በዚህም አመክንዮአዊ መስመር ስንሄድ የአማራ አንድነት ከአሰፋፈር ሁኔታውም ጋር የተያያዘ ነው እና ይህ አሰፋሩ ለሌሎች ምስለ አማራ ከሳች መለያዎች መሰረት ነው ልንል እንችላለን፡፡
መለክ ሐራ
===================================================
የአማራ ብሄረተኝነት መስመር (2: ታሪክ በብሄረተኝነት መነጽር*********************************************************


በተደጋጋሚ ከፋም ለማም የአማራ ታሪክ የአማራ ነው፤ ከሁለቱም በኩል ትምህርት ብቻ ነው መውሰድ ያለብን እያልን ለማስገንዘብ ስንሞክር ቆይተናል፡፡ አንድ ነገር በግድ መታወቅ አለበት፡፡ ታሪክን ለመናቆሪያነት መጠቀም ካሰብን ዘለአለም ስንጨቃጨቅ መኖር እንችላለን፡፡ ማለትም ላለመስማማት ከፈለግን መቸም አንስማማም፡፡ ይህም የሚሆነው በሶስት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛ ያለፈውን ታሪክ ሙሉ ስእል ማግኘት ስለማንችል እና የምንመረኮዝባቸው ሀቆች በሙሉ ሊደርሱን ስለማይችሉ፡፡ ሁለተኛ የአለፈን ጊዜ በአሁን ጊዜ መመንዘርና መፍረድ በአመዛኙ ስህተት በመሆኑ እና ብዙዎቻችን ለዚህ ሰለባ ስለምንሆን፡፡ ሶስተኛ በታሪክ ውስጥ ሆነ ተብሎም ይሁን ሳይተሳብበት የተሰሩ ስህተቶች የግድ አይቀሬ ስለሆኑ፤ ማለትም ታሪክን የሚሰሩት የሰው ልጆች በመሆናቸው ሰውን የሚያጋጥመው ውስንነትና ስህተት ታሪክ ላይም የግድ ስለሚንጸባረቅ፡፡ ስለሆነም ስለታሪክ ስንነጋር እነዚህን ነገሮች በቅድሚያ ግምት ውስጥ ማስገባት ይጠበቅብናል፡፡ ይህም የአማራን ታሪክ እና አሁን ከጀመርነው የብሄረተኝነት እንቅስቃሴ ጋር አዋህደን ለማራመድ ይጠቅመናል፡፡ ይህ ጽሁፍ በአመዛኙ ሰሞኑን ፌቡ ላይ ሲንሸራሸሩ ለነበሩ ሚዛናዊ ያልሆኑ እይታዎች እንደመልስነት የታሰበ ነው፡፡
ከዚህ በፊት የአማራ ብሄረተኝነት መስመር (1) ላይ የአማራ ማንነት ተገልጹዋል፡፡ የአማራ ታሪክ ተዋናዮች የሆነው ህዝብ በተለይም በታሪክ ላይ ሰፍረው የሚገኙት መሪዎችም ማንነታቸው ከዚሁ ከተጠቀሰው ሳይንሳዊ እሳቤ የሚወጡ አይደሉም፡፡ የአማራን ማንነት በቅጡ ካለመረዳታችን የተነሳ ይሄ ንጉስ አማራ አይደለም፤ ያ ንጉስ እትን ነው እያልን የራሳችንን ታሪክ ስንሸረሽር እንታያለን፡፡ መጀመሪያ አንድን ንጉስ ወይም ገዥ አማራ ነው ወይስ አይደለም ከማለታችን በፊት ስለአማራ ማንነት በጥቂቱም ቢሆን ማወቅ አለብን፡፡ የብሄረተኝነት እንቅስቃሴን እደግፋለሁ ወይም ቅርጽ እሰጠዋለሁ የሚል ሰው በመጠኑም ቢሆን ስለማንነት እንቅስቃሴዎችና መሰረቶች ማወቅ አለበት፡፡ ብሄረተኝነትን ለመቅረጽ መጀመሪያ ራስን ሰፋ አድርጎ መቅረጽ ያስፈልጋል፡፡ ይህ የተባለበት ምክንያት የብዙዎቹ ሰዎች ጽሁፎች ስህተት ወይም እውነት ናቸው ለማለት ሳይሆን የምንናገረው እውነትስ ሆነ ስህተት የተያያዝነውን የማንነት ፖለቲካ እንዴት ባለ መንገድ እና ሁኔታ እንደሚጠቅመው እና እንደሚጎዳው በደምብ እንዲታሰብበት ለማመላከት ነው፡፡
የብሄረተኝነት እንቅስቃሴ የወደፊት እቅድን የሚቀርጽ ሂደት ስለሆነ የወደፊቱን ለመቅረጽ የኋላ መነሻ ያስፈልገዋል፡፡ ብሄረተኝነት እንቅስቃሴዎች እንኳን ያለውን ታሪክ የሌለ አዲስ ነገር ይፈጥራሉ፡፡ የሰውን ቀልብ ማሰባሰብ እና ለአንድ አላማ አሰልፎ ግብን መጨበጥ የሚቻለው በሆነ አንኳር ወይም በሆኑ አንኳር ታሪካዊ ክስተቶች ዙሪያ ነው፡፡ ታሪክ በብሄረተኝነት እንቅስቀሴ ውስጥ እንደንብ አውራ (ንግስት) ነው፡፡ አውራው ወይም ንግስቲቷ የሌለችበት ንብ ይበተናል፡፡ ምክንያቱም አብሮ የሚያኖር ምክንያት ስለሌለው፡፡ እንደዚሁም የብሄረተኝነት እንቅስቃሴ አንድ ላይ አያይዞ ለአንድ ግብ የሚያሰልፍ ታሪክ ያስፈልገዋል፡፡ ከዚሁም በላይ የተጋጋለ ብሄረተኝነት ለማካሄድ የህዝቡን ያለፈ ታላቅነት መንገር የግድ ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ ያለበት ቦታ ላይ ሊወድቅ እንደማይገባው ደጋግሞ መንገር እና ያለፈው ትልቅነቱ እንዲናፍቀው ማድረግ ያሻል፡፡ ብሄረተኝነት የዛሬው ያለንበት ሁኔታ ውድቀት ነው ብሎ ነው የሚነሳው፡፡ ወደፊት ታላቅ ለመሆን መጀመሪያ ከታላቅነት መውደቅን ማመን ያስፈልጋል፡፡
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የሚወድ የእንትን ጠላት ነው ብለው የሚጽፉ ውስን ሰዎች አሉ፡፡ እንደአስተያየት ይከበርላቸዋል፡፡ ግን ነገርየው የማይጠቅም እና የእይታ ችግርን የሚያመለክት ነው፡፡ ንጉሱ እገሌን ግዛት በድለዋል ብሎ የሚያስብ ሰው እንደዛ ቢያስብ አይገርምም፡፡ በደል ከተባለ እንግዲህ ንጉሱ ላይ ሁሉም የሚነቅፍባቸው ይኖራል፡፡ እንግዲህ ዝም ተብሎ ሲታይ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ነገስታት የሚጠቀስ ጉድለት ይኖርባቸዋል፡፡ እነዛን ጉድለቶች ወይም አሉ የተባሉ ጉድለቶች ጠምዝዞ ለራስ አላማ ማዋል ግን ስህተት ነው፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የሚወድ የእንትን ጠላት ነው የሚለው ሀሳብ ግን እንደቀላል መታየት የሌለበት ነው፡፡ አንድ ሰው የአማራ ብሄረተኝነትን እደግፋለሁ ብሎ ሲያበቃ እንደገና ራሱን ከመላው አማራ ነጥሎ የተወሰነ አካባቢ ጠበቃ ካደረገ ጨዋታ ፈረሰ ማለት ነው፡፡ አንድ የአማራ ብሄረተኛ ስለራሱ ትውልድ ቦታ ብቻ የተለየ ስሜት ካለው እና ያንኑ ስሜቱን ሌሎቹም እንዲጋሩለት ከጠየቀ ይህ ሰው ትክክለኛ የአማራ ብሄረተኛ ነው ማለት አይቻልም፡፡ የሆነ አካባቢ ሰው ስለሆንኩ ብቻ ለአካባቢየ የተለየ ስሜት የሚሰማኝ ከሆነማ ሙሉ ኪሳራ ውስጥ ወደቅኩ ማለት ነው፡፡ አንድ የአማራ ብሄረተኛ የትም ይወለድ የትም አጀንዳው የግድ መላው አማራ ነው መሆን ያለበት፡፡ በአራቱ ግዛቶች፤ በሌላው ኢትዮጵያ እና በተቀረው አለም ተበትኖ የሚገኝ አማራ ሁሉ የእየለት ህይወቱ ሊያሳስበን እና በፍጹም አንድ እይታ ልንመለከተው ይገባል፡፡ አማራ ነኝ ስል የወሎም ሆነ የጎጃም ወይ የሸዋ አልያም የጎንደር ወይም በመላው አለም የተበተነው አማራ ህመም በእኩል ይሰማኛል ማለቴ ነው፡፡ በአማራ ብሄረተኝነት ውስጥ ሌላ ጭብጦ ይዞ መገኘት የብሄረተኝነቱ ነገር ያልገባው መሆንን ያመለክታል፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት ክፍለ ሀገራዊ ስሜት ራሳቸውን ከየትኛውም ክፍለ ሀገር ጋር ማያያዝ የማይችሉትን የተበተኑ አማሮች ያገላል፡፡ ታዲያ አንዱን አማራ የበለጠ እያሰብኩለት ሌላውን ሆነ ብየ ከረሳሁት ምን ዋጋ አለው!
እንዲህ አይነት የአማራን ብሄረተኝነት ለራስ ትውልድ ቦታ እንዲያጎበድድ መጣር በንኡስ ብሄረተኝነት እንጅ በአማራ ብሄረተኝነት መነጽር ሊታይ የማይገባው ነው፡፡ አመክንዮው ራሱ የሚገርም ነው እኮ፡፡ ቀኃሥን መውደድ በምንም መንገድ ከአንድ አካባቢ ጠላትነት ጋር አይያዝም፡፡ አንድ ሰው ስለየትኛውም አካባቢ ችግር ምንም ሳያውቅ ንጉሱን ሊወድ ይችላል፡፡ ያ ማለት ሳያውቅ እንኳ በጠላትነት ሊያዝ ነው ማለት ነው፡፡ እንደዛማ ከሆነ በየቤቱ የቀኃሥ ፎቶ የሌለው የለም እና ንጉሱን እጅግ ብዙ አማራ ይወዳልና ንጉሱን መጥላት ስለማይቻል የአማራ ብሄረተኝነት ከነአካቴው መቅረት አለበት ማለት ሊሆን ነው እኮ፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት ንኡስ ብሄረተኛነት ሌላ ንኡስ ብሄረተኝነትን ሊፈጥር እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እጅግ አጥብቄ የእኔ መንደር ባልኩ ቁጥር ሌላ የእኔስ መንደር የሚል ቡድን እየፈጠርኩ መሆኔን መረዳት ይገበኛል፡፡ በዛ ላይ ንጉሱ በጎም ሆኑ አልሆኑ ንጉሱ ላይ እጣት ከመቀሰር በፊት ንጉሱን እንዲህ ብል የእርሳቸው ደጋፊ ሊርቀኝ ይችላል፤ ብሄረተኝነቱም ሊጎዳ ይችላል ብሎ ማሰብም ያስፈልጋል፡፡
እንዲህ አይነቱ ንኡስ ብሄረተኝነት ጎጅ ነው፡፡ ምክንያቱም የብሄረተኝነት ዋና አላማው በማናቸውም ሰበብ ህዝቡን አንድ ላይ ማሰባሰብ እና አንድ አይነት ስሜት እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ እንዲህ አይነት የንኡስ ብሄረተኝነት አዝማሚያ ግን ህዝብን በአንድነት እንዳይቆም የመጋፋት አይነት ነገር ነው፡፡ በዛ ላይ ታሪክን ለመናቆሪያ መጠቀም የብሄረተኝነት ሌላው ተቃራኒ ጫፍ እንጅ ደጋፊ አይደለም፡፡ ከታሪክ ልንወስድ የሚገባው አንድነትን የሚያጎለብቱ እና የሚጠቅሙንን ብቻ ነው፡፡ ሌላውን በትምህርትነቱ እንይዘዋለን፡፡
ታሪክን በተመለከተ የአማራ ብሄረተኝነት በእውነት ላይ ብቻ መመስረት አለበት የሚለው አስተሳሰብ ስህተት ነው፡፡ በእርግጥ ብሄረተኝነት በእውነት ላይ ነው የሚገነባው፡፡ ያ ማለት ግን ብሄረተኝነት እንቅስቃሴ ፖለቲካ መሆኑን መርሳትን አያመለክትም፡፡ እውነት ብቻውን ፖለቲካዊ እቅስቃሴ ሊፈጥር አይችልም፡፡ እኛ የተያያዝነው የፍልስፍና ወይም የስነመለኮት ወይም የአካዳሚያዊ ታሪክ ትምህርት ክፍለጊዜን ማስፈን አይደለም፡፡ የአማራ ብሄረተኝነት ዋና አላማ ህዝብን በተገቢው ታሪካዊ ሀቆች ላይ በመመርኮዝ ለአንድ እጣ ፋንታ ማሰለፍ ነው፡፡ ታሪካዊ ጸጉር ስንጠቃውን ህዝባችን ነጻ ከወጣ በኋላ በመደበኛ የታሪክ ትምህርት ክፍለጊዜ እናስተምራለን፡፡ እውነትም ራሱ አንጻራዊ ነው እኮ፡፡ ቅንጭብ እውነት ይዘን የእውነት መጨረሻ ላይ የደረስንም ሊመስለን ይችላል፡፡ እውነትን ይዘን እንከራከር ብንል እንኳ እውነት በየደረስንበት የግንዛቤ ደረጃ ይወሰናልና እና ቋሚ መለኪያ አናገኝም፡፡ አንዱ እውነት ብሎ የያዘውን ሌላው በተጨማሪ እና ጥልቅ መረጃ ሊያፈርሰው ይችላል፡፡ ያም አለ ይህ የብሄረተኝነት አላማ እውነትና ሀሰት በሚል መነታረክ ሳይሆን ህዝብን በአንድነት ለተመሳሳይ አላማ ማቆም ነው፡፡ አማራ ህዝብ ትግል የህልውና መሆኑም መዘንጋት የለበትም፡፡
በአማራ ብሄረተኝነት ውስጥ የሞዐ አንበሣ አስተሳሰብ አያስፈልግም የሚል ደከም ያለ ነገርም ተጽፎ አይተናል፡፡ ቀኃሥን እንደሞዐ አንበሣ አድርጎ የማቅረብ ነገር ነው፡፡ ይን እንጅ ይህ የመረጃ እጥረት ነው፡፡ ቀኃሥ የሶሎሞናዊያን ስርዎ መንግሥት 225ኛ ንጉስ እንጅ ብቸኛ ንጉስ አይደለም፡፡ የሶሎሞናዊያን ስርወ መንግሥት ዋና አርማ ደግሞ ሞአ አንበሣ ነው፡፡ ስለዚህ ሞዓ አንበሳ በአርማነቱ የታሪካችን አካል እንጅ የአንድ ንጉስ ብቻ አሻራ አይደለም፡፡ ይሄንን ደግሞ መፋቅ አይቻልም፡፡
ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ የአማራ ጠላት ናቸው፡ አማራን ለማጥፋት ሰርተዋል የሚሉ ክሶችም ታይተዋል፡፡ እንግዲህ ቀኃሥ የአማራ ጠላት ናቸው፤ አማራን ሲያጠፉ ነው የኖሩ የሚለው ውንጀላ መሰረተ ቢስ ነው፡፡ እሳቸው እንደ አንድ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግስታዊ ሀላፊነቶችን ለሁሊም አካባቢ ለማዳረስ እና አገሪቷን ህዝቡ በአንድ ጥላነት እንዲቀበላት ጥረዋል፡፡ በተለየ ሁኔታ አማራን አጠፉ የሚለው አጉል ክስ ነው፡፡ በእርግጥ ተቀናቃኞቻቸውን አጥፍተዋል፡፡ ያ ደግሞ የፖለቲካው ባህርይ እንጅ የንጉሱ የተለየ አማራን የማጥፋት ፖሊሲ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡ ደግሞም አማራን አጠፉ የሚለውን ቃል ለእኝ ንጉስ መስጠት ጨካኝነት ነው፡፡ የተወሰኑ ተቀናቃኞችን ማፈናቸው ወይም ማጥፋታቸው አማራን ማጥፋት ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ በእርግጥ ስልጣናቸውን ለማማከል ወይም አሀዳዊ አገርን ለመፍጠር የየአውራጃና ጠቅላይ ግዛት ሹሞችን ሀይል አሳጥተው ማእከላዊ ጦር መስርተዋል፡፡ ይህ ሂደት እርሳቸው ያደረጉት ብቻ ሳይሆን ጣልያን በትልቁ አሻራውን ያሳረፈበት ነው፡፡ የየግዛት ሀይል ተዳክሞ በአንድ ማእከላዊ እዝ ስር የመውደቁ ሁኔታ ደግሞ የዘመኑ ሁኔታ ውጤት እንጅ የንጉሱ ብቻ መለኮት- መራሽ ስራ ውጤት አይደለም፡፡ እርሳቸውም እዛ ቦታ ላይ ባይሆኑ ሌላው ሊያደርገው የሚችለው ወይም በራሱ ጊዜ የሚሆን ክስተት ነው፡፡ የ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ በአማሮች የተከናወነ ነው፡፡ ያ ማለት ደግሞ ስልጣን ላይ አማሮች ነበሩ ማለት ነው፡፡ እንደጉድለት ከተቆጠረ ንጉሱ መኳንንትን ችላ በማለት ከተራው ህዝብ ወገን የሆኑ ሰዎችን ለወግ ለማእረግ አብቅተዋል፡፡ ግን አማራን ሆነ ብለው በደሉ የሚለው አያስኬድም፡፡
በመጨረሻም ነገስታቶቻችንን ከአማራ መነጠል ምን ጉዳት ያመጣል የሚለውን በቀጣይ የአማራ ብሄረተኝነት መስመር (3) እንመለስበታለን፡፡
መለክ ሐራ
===================================================
የአማራ ብሄረተኝነት መስመር (3): ነገስታቶቻችንን ከአማራነት መነጠል ምን ጉዳት ያመጣል?
******************************************************************


አንድ የአማራ “ተቆርቋሪ” ሰው በተደጋጋሚ አጼ ቴዎድሮስ “ቅማንት” ናቸው ብሎ ይናገራል፤ ኧረ እንዲያውም ይህንኑ ኑፋቁ በጥራዝ መልኩ ጸፎአል አሉ፡፡ ታዲያ አንዲት አማራ ትበሳጭና እስኪ ማስረጃ ትለዋለች፡ እርሱም እግዜርን ሳይፈራ ሰውንም ሳያፍር “የታንጉት ምስጢር” ላይ ነው ያነበብኩት ይላል፡፡ ይህ ሰው አጼ ቴዎድሮስን ቅማንት ለማድረግ የታንጉት ምስጢርን ምስክር መጥራቱ ብቻ አይደለም ችግሩ፡፡ ትልቁ ችግር ይህንን መጽሀፍ አለማንበቡ ነው፡፡ ሶስተኛው ችግር ደግሞ አጼ ቴዎድሮስን ቅማንት ናቸው ሲል አማራን እና ቅማንት አማራን አራርቆ ለማስቀመጥ መሞከሩ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ አጼ ቴዎድሮስ ቅማንት ናቸው የሚለው በራሱ ችግር አልነበረውም፡፡ ችግሩ ያለው በውስጡ ካዘለው ጸረ አማራ ፖለቲካዊ አጀንዳ ላይ ነው፡፡ እንጅማ ቅማንት አማራም ሆነ አማራ ያው አማራ ነው፡፡) ሌላኛው ችግር ደግሞ ለኢትዮጵያ ሲባል የአማራን ታሪክ ለማይፈልጉት ሁሉ መወርወር እና አማራን ታሪክ አልባ አድርጎ የማስቀረቱ ዘመን ያስቆጠረ ልማድ ቀጣይ ክፍል አራማጅ መሆኑ ነው፡፡ እግዜር ያሳያችሁ! ሌሎች ብሄሮችን ታሪክ እንዲሰሩ እና ከአማራ ጋር እንዲስተካከሉ ማድረግ ሲገባ የአማራን ዘርፎ አማራን ባዶ አድርጎ እነዛን ያልሰሩቱኑ ባለታሪክ ማድረግ! ይህንን የሚገልጽ አንድ ሌላ አማራዊ ገጠመኝ፡፡ በ1996 ዓ.ም. አማራ ከ8ኛ ክፍል በኋላ መማር የለበትም ተብሎ ፖሊሲ ወጥቶ ነበር፡፡ እስከ 8ኛ ክፍል ይማራሉ፤ ከዛ ወዲያ የራሳቸው ጉዳይ፡፡ ኦቦ አዲሱ ለገሰ ለምን እንዲህ ይደረጋል ተብሎ ተጠይቆ ሲመልስ “አማራ ከዚህ በፊት ስለተማረ ከሌሎች ጋር ለማስተካከል ነው” አይነት ንግግር ተናገረ፡፡ ገራሚ፡፡ ሌሎችን በማስተማር ከአማራ ጋር ማስተካከል ነው ወይስ አማራውን እንዳይማር ማድረግ ነው የሚገባው? ግን ቅንጅት መጥቶ የአማራን ወጣት ከዛ መከራ አተረፈው፡፡ ቅንጅት ለአማራ የዋለው ውለታ በዚህ ረገድ የሚረሳ አይደለም መቸም፡፡
ወደጥንተ ነገራችን እንመለስ፡፡ አንድ የብርሀኑ ዘርይሁን ጓደኛ የነበረ ሰው ብርሀኑ የታንጉት ምስጢርን እንዴት እንደጻፈው አጫውቶኝ ነበር፡፡ ብርሀኑ የታንጉት ምስጢርን ሲጽፍ የአዲስ ዘመን ስራ አስኪያጅ ነበር አለ፡፡ አንድ ጠረጴዛ ላይ በአንድ እጁ የታንጉት ምስጢርን ሲከትብ፤ በሌላ ወገን ተስተናጋጅ እና የስራ ባልደረቦች ስራ ሲሰጡት ደብተሩን እያጠፈ፤ እንደገና ስራና ሰው ቀለል ሲልለት ገልጦ እየጻፈ፤ እንደገና እየተዋከበ ነው የጻፈው አለ፡፡ ይህ ጓደኛየ ለብርሀኑ ዘሪሁን ያለውን አድናቆት ተናግሮ አይጠግብም፡፡ ብርሀኑ የታንጉት ምስጢርን በጻፈበት ውክቢያ ሁኔታ አይደለም መጽሀፍ የጋዜጣ አምድ ማዘጋጀት ፈታኝ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይናገራል፡፡ ለዚህ ጓደኛየ ብርሀኑ በቃ ብርቱ ሰው ነው፡፡ እና በዛ ወከባ ውስጥ ሆኖ የጻፈው መጽሀፍ እስከዛሬም ድንቅ ነው፡፡
ያው እንግዲህ መጽሀፉ ታሪካዊ ልቦለድ ነው፡፡ ታሪካዊ ልቦለድ በመሰረታዊ ጭብጥነት ታሪክ እና አፈ ታሪክ ላይ የሚመረኮዝ ቢሆንም በደራሲው ምናባዊ ተጽእኖ ስር ስለሚወድቅ ለታሪክ ማጣቀሻነት አይውልም፡፡ እንዲህ አይነቱ ድርሰት ደራሲው ተጨባጭ ታሪኮችን እና አፈ ታሪኮችን ልብ አንጠልጣይ በሆነ ሁኔታ የሚጽፍበት እንጅ የታሪክ ሰነድ አገላብጦ ማጣቀሻ አስቀምጦ እውነትን ብቻ የሚያስቀምጥበት አይደለም፡፡
ያም ሆኖ የታንጉት ምስጢር ውስጥ ላይ አጼ ቴዎድሮስ ቅማንት ናቸው የሚል አይገኝም፡፡ መጽሀፉ ራሱ የታንጉት ምስጢር የተባለበት ምክንያት የአጼ ቴዎድሮስ አባት ታንጉትን ከቅማንት አማራ መውለዳቸው እና በኋላም ይህችን ታንጉትን ወንድምዋ አጼ ቴዎድሮስ ለታማኛቸው ፊታውራሪ ገብርየ ሚስት አድርገው ማጋባታቸው እና በጋብቻውም ፍሬ ማፍራት ባለመቻላቸው አሁንም ቅድምም “ኧረ ባባጃሌው” የምትለዋ ወፍራም ሴትዮ (ስሟን ረስቸዋለሁ) ታንጉትን በመጀመሪያ ጭልጋ ወይኒ ኪዳነምህረት ጸበል መውሰድዋ (ይህ የወይኒ ኪዳነ ምህረቱ የጸበል ጉዳይ በአቤ ጉበኛ “አንድ ለእናቱ” መፅሀፍ ላይም በስፋት መገለጹ ይታወሳል)፤ በጸበል አልሳካ ሲል አምባ ጊዮርጊስ በሚስጢር ከአንድ የቆሎ ተማሪ ጋር እንድትተኛ ተደርጎ መጸነሱዋን እና ያንንም ወፍራሟ ሴት እና ታንጉት የገብርየ ልጅ ነው ብለው የማሳመናቸውንና የመሳሰለውን ውስብስብ የመንግስት ፖለቲካ ለማስረዳት ነው፡፡ የአጼ ቴዎድሮስ እህት ታንጉት በአንድ ወገን ከቅማንት አማራ ትወለዳለች፡፡ ነገር ግን አጼ ቴዎድሮስ እህቱ ቅማንት አማራ በመሆኑዋ ብቻ ቅማንት ነው ብለው የሚከራከሩ የአማራ “ተቆርቋሪዎች” ስናገኝ ያለንበት ዘመን እውነትም 8ኛው ሽህ መሆኑን በደምብ እንገነዘባለን፡፡ እዚሁ መጽሀፍ ላይ ፊታውራሪ ገልሞ የሚባል በጣም ጀግና ቅማንት አማራ ነበር፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ይህንን ጀግና ሰው “ምነው ሁሉም ቅማንት እንዳንተ በሆነልኝ” እያሉ ያንቆለጳጵሱት እንደነበር ብርሀኑ ጸፎአል፡፡ የማንቆለጳጰሱ ነገር የደራሲው ምናብ ይሁን እውነታ ወደጎን እንተወው እና ፊታውራሪ ገልሞ የሚባል በጣም ጀግና ቅማንት አማራ ከአጼ ቴዎድሮስ ጎን ከእነ ራስ እንግዳ እና ፊታውራሪ ገብርየ ጋር ተሰልፎ እንደነበረ ግን በታሪክ የሚታወቅ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ እስካሁን ድረስ አንድም አማራ ራሱን በፌስቡክ ራስ እንግዳ ብሎ በማስታወሻነት አለመሰየሙ አሳዝኖኛል)፡፡ አጼ ቴዎድሮስን ሀበሻ በሙሉ ከድቶ ከንጉሱ ጎን እስከመጨረሻው በታማኝነት ከቆሙት 5000 ወታደሮች አንዱ እና በጦርነቱም ለሚወደው ንጉስ እና ለቆመለት አላማ የተሰዋ ጀግና ነውና…. ራስ እንግዳ፡፡ ባጭር አገላለጽ ቅማንት አማራ የተበታተነውን አማራ ለማሰባሰብ በተደረገው እልህ አስጨራሽ የጀግንነት ስራ ከአጼ ቴዎድሮስ ጎን ሆኖ በህዝብ ሰብሳቢነት እና አገር አንድ አድራጊነት ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡
እንግዲህ አማራ ላለፈው ግማሽ ክፍለዘመን DeAmharization Process ውስጥ ያለ ህዝብ ነው፡፡ አማራን በዚህ ኢ-አማራ ማድረግ ሂደት ውስጥ የተሳተፉት በሚያሳዝን ሁኔታ አማራ ያልሆኑቱ ብቻ አይደሉም፡፡ አማሮቹ ራሳቸው በስፋት ተሳትፈውበታል፤ አሁንም እየተሳተፉበት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያንን በስሜትም በግብርም እንደ አንድ ሰው አሳቢ እንደ አንድ ልብ መካሪ ለማድረግ የእያንዳንዱን ብሄራዊ ማንነት ማጥፋት መልካም ሊመስል ወይም ሊሆን ይችላል፡፡ ደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ለጋዜጠኛ ዘነበ ወላ እንዳለው ፈረንሳዮች ኦምሌት ለመስራት እነቁላሉን መስበር ያስፈልጋል ይላሉ፤ አጼ ምኒልክም ኢትዮጵያን ለመፍጠር ወይም ኦምሌት ለመስራት እንቁላሉን መስበር ነበረባቸው፤ አጼ ምኒልክ እንቁላሉን ባይሰብሩት እና አማርኛን ባይሰጡን ኖሮ አንተ ከጋሞ እኔ ከትግራይ በምን እንግባባ ነበር ብለውት!
በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሁሉም እንቁላሎች ተሰብረዋል ማለት አይቻልም፡፡ ሌሎች እንቁላሎች እንዳሉ ሆነው አማራ ብቻ ተሰብሮ በስብርባሪው ሌሎችን እንቁላሎች እንዲያጣብቅ ነው የተደረገው፡፡ አማራ ተሰብሮ ሌላው ሳይሰበር የተሰራውም ኦምሌት ዛሬ የሌሎች አለመሰበር ህልውና እየተላወሰ እያየን ነው፡፡ የእነሱ ህልውናም አማራውን ጨርሶ ለማጥፋት ደርሷል፡፡ አሁን የተያያዝነው ሌሎችን እስከህይወታቸው ለማቆየት የተሰበረውን እንቁላል፤ አማራን፤ እንደገና መጠገን እና በብዙ ድካም ወደነበረበት መመለስ ነው፡፡ ኢትዮጵያን እንደ አገር እንደገና ለማቆም አማራ ብዙ ጊዜ ሲጨፈለቅ እና ሲሰባበር ነው የቆየው፡፡ በኋላም አማራ ማንነቱን ረስቶ ለኢትዮጵያዊነት ሲለውጥ ሌሎች ግን ስላልተሰባበሩ በነበሩበት ቆዩ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያዊነት ፕሮጀክት ሲጀመርም ሁሉንም ማንነቱን አሳጥቶ አንድ የማድረግ ሂደትን ያልተከተለ ነበር፡፡ ውጤቱንም አሁን እያየነው ነው፡፡ ያለፉት መሪዎቻችን፤ ልሂቃን እና አሁን ያለው ልሂቅ አማራን ብቻ ማጥፋት ኢትዮጵያን ይገነባል ወይም አጣብቆ ያቆያል ብለው ያስባሉ፡፡ በጣም ስህተት፡፡ ይህ ግን በአማራ ሞት ላይ ለሌሎች ያልተሰበሩ እንቁላሎች ህይወት መስጠት ነው፡፡ አማራ እየተሰባበረ ሌላው ግን ሲፈለፈል ቆይቷል፡፡ ስለሆነም አንዲት ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተደረገው ሂደት እና አሁንም እየቀጠለ ያለው ጥረት በአማራ ኪሳራ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም፡፡ ለአማራ ጎጅ ነው፡፡ አማራ ብቻውን ለምን ይሰበር!?
ስለዚህ ሚዛናዊ ባልሆነው እንቁላል ሰበራ የተዳከመውን የአማራነት ስሜት ለማጠናከር እየጣርን ባለንበት በአሁኑ ሰአት የተዘረፈብን እና እየተዘረፍብን ያለውን ታሪክ አለምንም መታለል እና መዘናጋት ማስመለስ ወይም መመለስ አለብን፡፡ አማራነታችን ለሌሎች የመስዋእት በግ ሆኖ በነጻ እንደታደለው ሁሉ የአማራ የሆነው ነገር ሁሉ እንዲሁ በገፍ ተዘርፏል፡፡ ከላይ የኦቦ አዲሱ ለገሰ ምሳሌነት እንደሚያስረዳው አይነት ነገር ነው አማራ እና አማራነት እንዲሁም የአማራ የሆነው ሁሉ ላይ እየተካሄደ ያለው፡፡ በጣም በሚያናድድ መልኩ እኛም ራሳችን ሳናውቅ ወይም በግብዝነት ይህንን የአማራ የሆነውን ሁሉ ፍቆ የማጥፋት እና ለሌሎች የመሸለሙ ስራ ላይ በአጋዥነት ስንሰራ እንታያለን፡፡
ከላይ በአጼ ቴዎድሮስ ላይ የቀረበው የታንጉት ምስጢር አይነት ምስክር በአጼ ምኒልክና በአጼ ኃይለ ሥላሴ ላይ በስፋት ሲንጸባረቅ ይታያል፡፡ ለምሳሌ በመግቢያየ የጠቀስኩት የአማራ “ተቆርቋሪ” አጼ ምኒልክን እና አጼ ኃይለ ሥላሴን ከአማራነት ፍቆ ለሌላ አስረክቧል፡፡ ያው ማስረጃው መሰለኝና ደሳለኝ ቢሆንም ቅሉ! ማን ይሰማዋል! በተመሳሳይ እዚሁ ፌስቡክ ላይ በአማራ ብሄረተኝነት አምናለሁ የሚል ራሱን ካይማር ሠርፀ ድንግል ብሎ የሚጠራ ሰው አጼ ኃይለ ሥላሴን አማራ አይደሉም ብሏል፡፡ በጣም የሚገርመው ይህ ሰው ጉራጌን አማራ ነው ብሎ ያምናል፡፡ በዚህ ሰው አባባል ለምሳሌ በቅርቡ ብርጋዴር ጀኔራል ተስፋየ ሀብተማርያም ጉራጌ አማራ ሲሆን ከወሎ የተወለደውን የሻእብያና ኦነግ መጠቀሚያ የነበረውን ዋለልኝ መኮንንን በበረራ ልዩ ሀይልነቱ መግደሉን አወድሶ ጽፎአል፡፡ ነገር ግን አጼ ሀይለስላሴ አማራ አይደሉም የሚባልበት ምክንያት አንዱ ጉራጌ ደም አላቸው የሚለው ነው፡፡ ጉራጌን አማራ ያለ ሰው ታዲያ ከጉራጌ እና አማራ ተወለደ የተባለን ንጉስ እንዴት ብሎ ነው አማራ አይደለም የሚለው!!!!? በነገራችን ላይ አጼ ኃይለ ሥላሴ የጉራጌ ደም አላቸው የሚለውን በቂ ማስረጃ የለኝም፡፡ እንደማስረጃ የምጠቅሰው የታጋይ አንዳርጋቸው ጽጌን “ነጻነትን የማያውቁ ነጻ አውጭዎች”ን ነው፡፡ ታጋይ አንዳርጋቸው እዛ ላይ ቃል በቃል “በአጼ ምኒልክና አጼ ኃይለ ሥላሴ የደም ቧንቧ ከሚፈሰው የአማራ ደም ይልቅ የኦሮሞና ጉራጌ ደም ይበልጣል” ብሏል፡፡ ከየት እንዳገኘው አላውቅም፡፡ ይሁንና ይህም አባባል የተጠቀሰው ኢ-አማራ የማድረጉ ሂደት (DeAmharization Process) አንዱ አካል ነው፡፡
እንግዲህ ጉራጌ፤ ሀድያ፤ ከምባታና አደሬ በኦሮሞ ወረራ ከጥፋት ከተረፉት የጥንት የአማራ ክፍሎች የሚጠቀሱ መሆናቸው አያከራክርም፡፡ አጼ ምኒልክም ሆኑ አጼ ሀይለ ሥላሴ የጉራጌ ደም ቢኖራቸው አማራነታቸው እንደተጠበቀ ነው፡፡ እንደዋዛ መታለፍ የሌለበት ግን እነዚህ ነገስታት የኦሮሞ ደም አላቸው የሚለው የክህደት ነገር ነው፡፡ አጼ ምኒልክ የኦሮሞ ደም አላቸው የሚለው ነጭ ውሸት ነው፡፡ የዘር ሀረጋቸውን የንጉሱ ጸሀፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ “ታሪከ ዘመን ዘ ዳግማዊ ምኒልክ” በተሰኘው መጽሀፋቸው በተገቢው ዘርዝረው ጽፈውታል፡፡ እዛ ላይ መመልከት ነው፡፡ አጼ ኃይለ ሥላሴ ኦሮሞ ደም አላቸው የሚለው በጥልቀት መታየት አለበት፡፡ እንደሚባለው በአያታቸው ከሀረር ኦሮሞ ይወለዳሉ ነው፡፡ መልካም፡፡ ነገር ግን ኦሮሞ በሁለት ይከፈላል፡፡ ኦሮምኛ ተናጋሪ አማራ እና ኦሮሞ ተብሎ (ቢያንስ ከዚህ ጽሁፍ አንጻር)፡፡ እንደሚታወቀው የሀረር ኦሮሞ ኦሮምኛን ለረዥም ጊዜ በመናገሩ ወደኦሮሞነት የተቀየረ የጥንት አማራ ነው፡፡ ይህንን መሰል ጉዳይ የጀነቲክስ (ዘረመል) ጥናቶች እያፍታቱት ነው፡፡ ለወደፊቱም ኦሮምኛ በመናገር ብቻ ኦሮሞ መስሎት የሚኖረውን የጥንት አማራ ወገናችንን በዚህ መሰል ሳይንሳዊ ዘዴ ነው ወደቀደመ አማራ ማንነቱ የምንሰበስበው፡፡ ይህም ማለት አጼ ኃይለ ሥላሴ በአያታቸው ኦሮሞ ናቸው ቢባል እንኳ በዚህ መንገድ ኦሮምኛ በመናገር ላይ ከሚገኝ ከጥንት አማራ የተወለዱ አማራ ናቸው ማለት ነው (He descends from a culturally Oromo but a genetically Amhara population)፡፡ ስለዚህ አጼ ኃይለ ሥላሴ አማራ ብቻ ናቸው፡፡
ቢባል ቢባል እና አጼ ኃይለ ሥላሴ ኦሮሞ ደም አላቸው ብንል እንኳ ሊሆኑ የሚችሉት በአንድ አያታቸው ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት 75% አማራ ናቸው ማለት ነው፡፡ በጀነቲክ ሳይንስ ደግሞ 25% is recessive while 75% is dominant gene. ይህ ማለት 25 ከመቶው ጅን በ75 ከመቶው የተሸፈነ ወይም ዋና ያልሆነ፤ የዘር ሀረግን በዋናነት ማስተላለፍ የማይችል፤ ለራሱ የተወሰነ ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው 75 ከመቶው የወረሰበትን ወላጅ ዘር ሙሉ በሙሉ ይይዛል ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ግማሹ ወይም 50 ከመቶው አማራ ቢሆን እንኳ አማራ ነው እንኳን 75 ከመቶው! እንዳለመታደል ግን ለግማሽ ክፍለ ዘመን ከዘለቀው የኢ-አማራ ማድረግ ሂደት የተነሳ አማራን ኦሮሞ ለማድረግ 25 ከመቶ በቂ ነው፡፡ 75ን ለ25 በግድ እጁን ጠምዝዞ ማስረከብ! በእናንተ በራሳችሁ ክርክር እንኳ 75 ከመቶ የሆነን ሙሉ አማራ ለ25 ከመቶው አሳልፋችሁ ለመስጠት የምትንጦለጦሉ አማራ ተብየዎች ማፈር አለባችሁ፡፡ ያም አለ ይህ አጼ ኃይለ ሥላሴ ከፍ ዝቅ የሌለባቸው አማራ ናቸው፡፡ እዚህ ጋር የተጠቀሰው ጀነቲክ ማብራሪያ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ደግሞ ንጉሱ በባህል ሙሉ በሙሉ አማራ ናቸው፡፡ ማለትም አንድን ህዝብ ከዘሩ በተጨማሪ አማራ የሚያደርገው ሳይንሳዊ የባህል ማብራሪያ ነገሮችን ሙሉ በሙሉ፤ አንድም ሳያጓድሉ የያዙ ንጉስ ናቸው፡፡ ኧረ በበለጠ ሁኔታ፡፡
በነገራችን ላይ ካይማር እና አክናሁስ “አጼ ሀይለ ስላሴ በታሪክ ፊት ብላችሁ” ስለፓኪስታን ምናምን የምትዘባርቁትን ሀሜት አይቸዋለሁ፡፡ ያው ሀሜት ከሀሜትነቱ አይዘልም…ታውቃላችሁ ወይም ታውቃለህ፡፡ የፓኪስታኑ ጉዳይ አስጨንቆኝ ሳይሆን አንድ ምክር ለመለገስ ነው ያንን ትርኪ ምርኪ ሀሳባችሁን ያነሳሁት፡፡ ይህንን ሀሳብ የሚያራምዱትን ዋነኞቹን የጀርመን ፕሮፌሰሮች አውቃቸዋለሁ፡፡ እዛ ትግራይ አካባቢ ያስተምራሉ፤ ሪሰርች ይሰራሉ፡፡ ለአማራ ያላቸው ክፉ አመለካከት ግን ከአንድ የአድዋ ተወላጅ ወያኔ ቢብስ አንጅ አያንስም፡፡ አንዱ በተለይ ትግሬን ደግፎ እዚህች አገር ላይ ለደረሰው ችግር ሁሉ አማራን ተጠያቂ አድርጎ የሚከራከር ነው፡፡ ስለፓኪስታኑ ጉዳይ ሲያራግብ ማስረጃ አምጣ ስለው ንጉሰ ራሳቸው የጻፉት ጽሁፍ ላይ የሆነ ፎቶ አይቸ ምናምን ነው የሚለው፡፡ ሌላም የሚዘባርቀው ነገር አለ፡፡ ግን አላማው የወያኔን ጸረ አማራ ስራ ማገዝ ነው፡፡ ይህንን ስላችሁም ዝም ብየ አይደለም፡፡ የጀርመን ምሁራን ለኦነግ፤ ሻእብያና ወያኔ በትጥቅ ትግል ወቅት የፕሮፓጋዳ ድጋፍ ያደርጉ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ዘነበ ፈለቀ “ነበር” ብሎ በጻፈው መጽሀፍ ውስጥ ደርግ ሁለት የደህንነት ሰራተኞችን ወደምእራብ ጀርመን መላኩን፤ የደህንነቶችም ተልእኮ አንድ የሸማቂዎች ዋና ሰውን ለመግደል እንደነበረ፤ ነገር ግን አንደኛው ደህነነት ቦምቡን በመጽሀፍ መልክ ለማጥመድ እየሰራ በነበረበት ጊዜ ሌላኛው ደህንነት ውጭ ቆይቶ ድንገት ወደክፍላቸው ሲገባ ሳያስበው ቦምቡን ነክቶት መፈንዳቱን፤ ያንንም ተከትሎ ይህንን ከፍንዳታ የተረፈ ደህንነት የምእራብ ጀርመን የደህነነት ሰራተኛ አይኑን ደንቁሎ አውጠቶ ጥሎት ወደአዲስ አበባ መመለሱን እንደጻፈ ነገርኩት፡፡ ይህም ፕሮፌሰር “ደርግ የላካቸው እነዛ ደህንነቶች ማንን ለመግደል እንደነበር አውቃለሁ፤ ለተቃዋሚዎች የፕሮፓጋንዳ ድጋፍ ያደርግ የነበረን ጓደኛየን ለመግደል ነበር” ብሎ ነገረኝ፡፡ እና ምን ማለት ፈልጌ ነው፡- አጼ ኃይለ ሥላሴን ኢ-አማራ ማድረግ ወይም አማራ ላይ መዝመት የዚህ አገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን አለማቀፍ ተልእኮም አካል ነው እያልኳችሁ ነው፡፡ ሀሜትን እንደማስረጃ በማቅረብ ወይም ማረጋገጥ የማትችሉትን ወሬ በማዛመት አማራነታችንን ከመጉዳት እንድትታቀቡ ለማሳሰብም እወዳለሁ፡፡
ከላይ በተጠቀሰው መልኩ እየተደረገ ያለው ነገስታቶቻችንን ኢ-አማራ ማድረግ ምን ጉዳት ያመጣል የሚለውን እንመልከት፡፡ አማራ የሆኑትን ነገስታቶቻችን አማራ አይደሉም ስንል ብዙ ነገር እናጣለን፡፡ ዋና ዋናዎቹም አምሐራ ነጻ ህዝብ ነው ስንል አማራ ከጥንት ጀምሮ እስከ ዘመነ ቅኝ ግዛት ድረስ በማንም ተገዝቶ አያውቅም ማለታችን ነው፡፡ በአለም ደረጃ ቅኝ ያልተገዛች ኢትዮጵያ ሲባል የዚህ ድል ዋናው ተዋናይ አማራ ነው፡፡ የማእከሉ ማእከል ላይ ደግሞ አማራ ነገስታት ይገኛሉ፡፡ አጼ ቴዎድሮስ አማራን በማሰባሰባቸው በኋላ የመጡትን ወራሪዎች በአንድነት እንዲመክት እድል አመቻቹ፡፡ ይህንን አጼ ቴዎድሮስ የሰበሰቡትን እና በሀይለኛ ክንድ ደቁሰው አንድ ያደረጉትን አማራ በመጠቀም ዳግማዊ ምኒልክ የበለጠ በማጠናከር የመከላከያ ወረዳቸውን አስፋፉበት፤ የተወሰደውንም መሬት መለሱበት፡፡ የመከላከያ ወረዳ ማስፋት ምን ማለት ነው? ንጉሱ የጥንት ግዛታቸውን ከማስመለስ ባለፈ ዙሪያቸውን በስፋት ከያዙበት ምክንያቶች አንዱ ቅኝ ገዥዎች ምናልባት ወደመሀል እንምጣ ቢሉ እዛው በረዥም ዳርቻ ለመከላከል በማሰብ እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡ ከጅቡቲ ወይም ሀርጌሳ ተነስቶ የሚመጣ ሀይል መሀል ኢትዮጵያ ወይ አማራ ላይ ከመድረሱ በፊት መከላከል ይቻላል፡፡ በጋምቤላም በሩዶልፎ (ደቡብ፡ ኬንያም) እንዲሁ ነው፡፡ ይህን የተስፋፋ የመከላከያ ወረዳ በመጠቀም እና ሰፊው ግዛት የፈጠረውን አቅም በመጠቀም በወራሪዎች ላይ አለም አቀፍ ድል ተጎናጸፉ፡፡ አጼ ኃይለ ሥላሴም በበኩላቸው ከዚህ ታላቅ ንጉስ የተረከቡትን አገር እና ነጻነት ለማስጠበቅ በነፍጥ ተፋልመዋል፡፡ አልሆን ሲልም ወደ ውጭ ሄደዋል፡፡
እዚህ ላይ ንጉሱ ወደውጭ መሄዳቸውን እንደሽሽት የሚቆጥሩ አሉ፡፡ ይህ ግን ውሀ የማያነሳ ክርክር ነው፡፡ አምባሳደር ብርሀኑ ድንቁ “ቄሳርና አብዮት” በተሰኘች መጽሀፉ ይህንን ነገር በሚገባ አብራርቶታል፡፡ ብርሀኑ ድንቄ ለመከራከሪያነት ያቀረባቸው ጭብጦች የአጼ ኃየለ ሥላሴን ከአገር መውጣት እና የአጼ ቴዎድሮስን መቅደላ ላይ መሰዋት ነው፡፡ እንደ ብርሀኑ ድንቄ አባባል ለአንድ አይዲያሊስቲክ ኢትዮጵያዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ማይጨው ላይ ራሳቸውን ማጥፋት ነበረባቸው፤ ራሳቸውን ቢያጠፉ ትክክል ናቸው፡፡ በሌላ ጎኑ ለአንድ ፕራግማቲክ ሰው አጼ ኃይለ ሥላሴ ሁኔታው እንደማይሆን ሲያውቁ አገር ለቀው መሰደዳቸው ተቀባይነት አለው፡፡ እዚህ ጋር ክርክሩ በአይዲያሊስት እና ፕራግማቲስት ተቃርኖዎች ላይ ነው፡፡ ማለትም አንድ አይዲያሊስት የአጼ ኃይለ ሥላሴን ድርጊት ኮንኖ ሊከራከር ይችላል፡፡ በሌላ ወገን አንድ ፕራግማቲስት ግን የንጉሱን ድርጊት ደግፎ ሊከራከር ይችላል፡፡
በአጭር አገላለጽ ምን ማለት ነው፡- ንጉሱ መሰደዳቸው ተጨባጭ ለውጥ አምጥቶአል፡፡ ንጉሱ እዛው ላይ ሞተው ቢሆን እና ጣልያን ተቆጣጥሮን ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ ወይም የአማራ ነጻ ህዝብነት ወይም አምሐራነት አከተመ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ንጉሱ በመሰደዳቸው የኢትዮጵያ ስልጣነ መንግስት አብሮ ተሰደደ ማለት ነው፡፡ ያ ማለት የኢትዮጵያ መንግስት ከአገሩ ተሰዶ በሌላ አገር በስደተኝነት ቀጥሎ ነበር ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ንጉሱ አገራቸውን እንጅ ስልጣናቸውን አልተቀሙም፡፡ ዙፋናችንም አልተወገደም፡፡ ንጉሱ በስደት መንግስታቸውን ይዘው በመሰደዳቸው ኢትዮጵያ በጣልያን ስር ሆናም የመንግስትዋ ህልውና አላከተመም ነበር፡፡ ይህ በራሱ ትልቅ ጥቅም አምጥቷል፡፡ ንጉሱ በስደት ሆነው ዲፕሎማሲያዊ ትግል በማድረግ የአላይድ ፓወርስ ድጋፍ ማግኘት ችለዋል፡፡ ያም ድጋፍ በኋላ ከአርበኞች ትግል ጋር ተደማምሮ በስደት የነበረውን መንግስት ተመልሶ በቦታው እንዲተከል አድርጎታል፡፡ አገር ውስጥ ይደረግ የነበረው የአርበኝነት ትግልም ይህንን የንጉሱን ዲፕሎማሲያዊ ትግል ለማገዝ ረድቶአል፡፡ እዚህ ላይ የንጉሱን ዲፕሎማሲያዊ ትግልና ያም ትግል ያስገኘውን አለማቀፍ ድጋፍ ለማሳነስ ሲል አርበኞች ነጻ ሊያወጡን ይችሉ ነበር ብሎ ሊያስብ ይችላል፡፡ እኔ ግን የአርበኞች ትግል ብቻውን ነጻነታችንን ያጎናጽፈን ነበር ብየ ለማሰብ ይከብደኛል፡፡ በምንም መልኩ የአርበኞች ተጋድሎ ወደር የለሽ መሆኑ የታመነበት ነው፤ ይሁንና የንጉሱ ዲፕሎማሲያዊ ትግል የላቀውን ሚና ተጫውቷል ብየ አስባለሁ፡፡ ለምሳሌ Michela Wrong “I didn’t Do It For You” በተባለው መጽሀፏ ውስጥ የንጉሱ ቀኝ እጆች የነበሩት የሲልቪያ ፓንክረስት ቤተሰቦች በተለይም ሲልቪያ ፓንክረስት የነበራትን ተደማጭነት በመጠቀም በየአገሩ እየዞረች ለንጉሱ ድጋፍ ታሰባስብ ነበረች፡፡ የድጋፉም አይነት የዲፕሎማሲ እና የገንዘብ ነበር፡፡ በዚህም ብዙ እንግሊዛዊያንን እና ከዛም አልፎ ሌሎች አውሮፓዊያንን ከንጉሱ ጎን ማሰለፍ ችላለች፡፡ ግን ደርግ ንጉሱን ለማጥላላት ብዙ ሰርቷል፡፡ የዛም ክፉ ፕሮፓጋንዳ ቅሪት በወያኔ ህይወት ተዘርቶበት ወደራሳችን ወገኖችም ተጋብቶ እስከዛሬ ድረስ አለ፡፡
ስለዚህ የነገስታቶቻችን አማራነት ከጣልን አምሐራ ነጻ ህዝብ ነው የምንለውን አብረን መጣል አለብን፤ ኢትዮጵያ ወይም አማራ ቅኝ አልተገዙም የሚለውን መወርወር አለብን፤ የጥቁር ዘር አንጸባራቂ የሆነ አለማቀፍ ድል ሲያደርግ ዋነኛው ህዝብ አማራ እና መሪዎቹ አማራ ነገስታት መሆናቸውንም መጣል አለብን፤ እነደአማራነታችን የወረስነውን አኩሪ ገድል ሁሉ አብረን መጣል አለብን ማለት ነው፡፡ አንዱን የአማራነት አሻራ ስንጥል ሁሉንም እየጣልን እንደሆነ ማወቅ አለብን፡፡ በራሳችን ነገስታት ላይ ስንዘምት በራሳችን ላይ እየዘመትን መሆናችንን እንገንዘብ፡፡ አማራነታችንን ሌሎች የሚሸራርፉት እና የሚያጠፉት ይበቃል፡፡post Amhara rise
መለክ ሐራ [Melek Hara] Thank you the Enlightened

No comments:

Post a Comment